
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም እና ሰላማዊነት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይኾን ለፍጡራን ሁሉ አስፈላው እና ቀዳሚው ጉዳይ ነው።
ከሰላም እና ሰላማዊነት የማያተርፍ ቢኖር እሱ ከመጥፎ ተግባራት የተጣባ ነው። በጎ ያልኾኑ ተግባራትን የሕልውና ጉዳያቸው የሚያደርጉ አካላት ሁሌም ከሰላም በታቃራኒ የቆሙ ናቸው።
ስለምን ሰላም ዋጋ ተነፈጋት? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት የሕዝብን ሰላም ሲያውክ ቆይቷል። ሰላምን የሚሹ ሁሉ ወገኖች በሰላም እጦት እና ናፍቆት ውስጥ ናቸው። የሰላም አለመኖር ምን ያህል ከባድ እንደኾነ ትክክለኛው ምላሽ ያለው የሰላም እጦቱ ዋጋ ያስከፈላቸው ዜጎች ውስጥ ነው። እውነተኛው ምላሽ ያለው የምትወደው ልጇ እንደወጣ በቀረባት እንስፍስፍ እናት አንጀት ውስጥ ነው።
ዳሩ ምን ያደርጋል ለሰላም ዋጋ መስጠት ችላ የተባለ ነው። ስለ ሰላም ሲባል መነጋገርን፣ ለሰላም መሸነፍን ባሕል ማድረግ ላይ ክፍተት አለ።
ከሰሞኑ በደቡብ ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተፈጠረው ግጭት፣ የደረሰው ጥፋት እና የንብረት ውድመት የዚህ ዋነኛ አስረጅ የሚኾን ነው።
የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪው የእድሜ ባለጸጋ ግጭቱን አስመልክተው ሀሳባቸውን ለአሚኮ አጋርተዋል። “በዕድሜየ ብዙ ክፉ እና ደግ ነገር አይቻለሁ፤ አሁን እየኾነ ያለው ግን ግራ የገባው መተላለቅ ነው። ወንድም ከወንድሙ እንዲህ ሲገዳደል ከማየት ምነው በጊዜ በሞትኩ ብያለሁ” ነው ያሉት።
ተወልጀ ባደኩበት ደብረ ታቦር ከተማ ይህን አጸያፊ ተግባር በማየቴ አሳዝኖኛል ብለዋል። የሚወዷትን ከተማ ባወደሙ አካላት ላይም ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ልጆቻችን ስለምን መደማመጥ ተሳናቸው? በማለት ጠይቀዋል። እየደረሰ ባለ ውድመት እና ግድያ ከንፈር እየመጠጡ መኖር ትናንት በታሪክ ሲጠቅም አላየሁትም ዛሬም አያድነንም ነው ያሉት።
መፍትሔው ወደ ቀልብ መመለስ ነው ብለዋል። ሕዝብ የመፍትሔ አካል መኾን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ሌላው ሃሳባቸውን የገለጹት የሃይማኖት አባት በሃሳብ መግባባት ባይቻል እንኳን ታሪክን እና የራስ ሃብትን በእሳት ማጋየት ምን ይሉት ብሂል ነው? ብለዋል። ጥቅም አልባ ድርጊት መኾኑንም ገልጸዋል።
ለሀገር እታገላለው የሚል አካል ታሪክን እና ሃብቱን ካወደመ የሚመራው ምኑን ይዞ ነው? በማለትም ይጠይቃሉ። በሌለ አቅም የተገነቡ የጤና ተቋማትን፣ የሕክምና መድኃኒትን እና ታሪክን ማውደም ይቅር የማይባል ጥፉት ነውም ብለዋል።
“ሺህ ዓመት ለማንኖርባት አጭር ዓለም እውነትን ተናግሮ ከመሸበት እንደር፤ ሰላም የሚሰፍነውና ለሁሉም ነገር መፍትሔ የሚገኘው እውነት ላይ ስንቆም ነው” ይላሉ። በሕዝብ መካከል እየኖረ ግጭት የሚጠምቅን አካል በጋራ መታገል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የራስን ታሪክና ሃብት በእሳት ማውደም ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል አካል አይጠበቅም፤ ሁሉም በድፍረት ተነጋግሮ ጥፋትን ማስቆም አለበት ብለዋል።
ዝምታ ይሰበር፤ እውነትም ይውጣ፤ ያኔ ሰላም ይኾናል ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
