ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ እሸጋ እና ስርጭት መጀመሩ ተገለጸ።

8
አዲስ አበባ፡ የካቲት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚያስፈልጉ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶችን የማሸግ እና የማሰራጨት ተግባር እያከናወነ መኾኑን አስታውቋል። ቦርዱ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ ዝግጅትን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጠው ማብራሪያ እና ባካሄደው የመጋዘኖች ጉብኝት እስካሁን ባለው ሂደት 40 በመቶ የሚኾነው የማሸግ ሥራ መጠናቀቁን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሎጅስቲክስ ኀላፊ መላከ አሉላ እንደገለጹት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የተገዙ ቁሳቁሶች በአዲስ አበባ በሚገኙ ሦሥት ግዙፍ መጋዘኖች ውስጥ ለስርጭት እየተዘጋጁ ይገኛሉ። የመራጮች ምዝገባም በእጅ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ኾኖ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
እንደ ኀላፊው ገለጻ ለምዝገባው ሁለት አይነት ቀለም ያላቸው ሳጥኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ።ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ሳጥኖች በተለመደው በእጅ ለሚከናወን ምዝገባ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን የያዙ ናቸው። ሃምራዊ ሳጥኖች ደግሞ በቴክኖሎጂ ወይም በታብሌት ለሚከናወን ምዝገባ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን እና ታብሌቶችን ያካተቱ ናቸው።
እነዚህ ሳጥኖች የመራጮች መዝገብ፣ ካርድ፣ የተለያዩ ፎርሞች፣ 27 አይነት ባነሮች እና ወረቀቶች፣ የግንዛቤ መፍጠሪያ ፖስተሮች፣ የቅሬታ አፈታት መመሪያ እና ቁልፎችን ጨምሮ ሰባት አይነት መሠረታዊ ቁሳቁሶችን ይዘዋል።
በዝግጅቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ 52 ሺህ 720 የምርጫ ጣቢያዎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል። የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ከዚህ ቀደም ከነበሩት አምስት ቋንቋዎች በተጨማሪ አዲስ የሲዳምኛ ቋንቋን አካተው ተዘጋጅተዋል።
እስከ የካቲት 12/2018 ዓ.ም ድረስ 22 ሺህ የሚጠጉ ሳጥኖች ታሽገው መጠናቀቃቸው ተመላክቷል።
በመጭው እሑድ የካቲት 15/2018 ዓ.ም የማሸግ ሥራው ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ነው ያሉት። ለስርጭት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሩቅ ስፍራዎችም ተለይተዋል ብለዋል።
የቁሳቁሶቹን ደኅንነት የማስጠበቅ ኀላፊነት በፌዴራል ፖሊስ ተይዟል። የጥራት ማረጋገጥ ሥራው ደግሞ በኢትዮጵያ ፓስታ አገልግሎት እየተከናወነ ይገኛል። ስርጭቱ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በየብስ እና በአየር ትራንስፖርት የሚከናወን ነው ተብሏል። እንደ ጋምቤላ ክልል አኮቦ ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ በጀልባ አማካኝነት ቁሳቁሶቹ እንደሚጓጓዙ ታውቋል።
ከየካቲት 17/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚሰጠው የምርጫ አሥፈጻሚዎች ሥልጠና የሚያስፈልጉ 7 ሺህ ሳጥኖች ዝግጅትም ጎን ለጎን እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በጽናት መቆም ያስፈልጋል።
Next articleሴቶች በቂ የውክልና ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል።