የኩፍኝ በሽታ ምንድን ነው?

7
‎ባሕር ዳር: የካቲት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ከሰሞኑ በብዙ ሕጻናት ሰውነት ላይ የሚታየው ሽፍታ እና አብዛኛው ምልክቱ ከኩፍኝ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነገር ሲታይ ተስተውሏል። በሕጻናት ላይ የታየው ነገር ኩፍኝ ነው ወይስ?
👉 የኩፍኝ በሽታስ ምንድን ነው?
‎ኩፍኝ ሚዝልስ በሚባል ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው ያሉን በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎች እና የጤና ሁኔታዎች ቡድን አሥተባባሪ ጽጌረዳ አምሳሉ ናቸው።
‎በሽታው ክትባት ባልወሰዱ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ባሉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሲኾን በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናትን እንደሚያጠቃ ተናግረዋል።
‎የበሽታው ምልክቶችም በሰውነት ላይ ደቃቅ ሽፍታ፤ ትኩሳት፣ የዓይን መቅላት እና የአፍንጫ ፈሳሽ መኖር ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል። ለሳምባ ምች እና ለሌሎች በሽታዎች እንደሚያጋልጥም ጠቁመዋል።
‎ኩፍኝ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው፤ በበሽታው የተያዘ ሰው በሚስልበት፣ በሚያስነጥስበት እና በሚያወራበት ጊዜ በትንፋሽ አማካኝነት ወደ ሌላ ሰው ይተላለፋል ብለዋል፡፡ ቫይረሱ በአየር ላይ እስከ ሁለት ሰዓት የመቆየት አቅም ስላላው ታማሚው በነበረበት ቦታ ያሉ ሰዎችን ያጋልጣል ነው ያሉት።
‎ሽፍታ ዋና ምልክቱ በመኾኑ ከሌሎች እንደ ሩቤላ እና ቺክን ፖክስ (በተለምዶ ጉድፍ) ከሚባሉ በሽታዎች ጋር ስለሚመሳሰል ኩፍኝ መኾኑን ለማረጋገጥ በደም ናሙና በላበራቶሪ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
‎የኩፍኝ በሽታ ዋነኛ መከላከያ መንገዱ ክትባት መኾኑንም ተናግረዋል። የኩፍኝ ክትባት በመደበኛነት ለሕጻናት በዘጠኝ እና በ15 ወር እንደሚሰጥ የተናገሩት አሥተባባሪዋ በተወሰኑ ዓመታትም በዘመቻ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
‎የበሽታው ምልክት የታየበትን ሰው በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ በሽታው ተለይቶ ሕክምና ማግኘት አለበት ነው ‎ያሉት። በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ ከተከሰተም ክትባት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። ክትባት የወሰዱ ሕጻናት ላይ በሽታው ቢከሰትም እንኳ በቀላሉ ይድናሉ ብለዋል። ያልተከተቡት ግን የሕክምና እርዳታ ካላገኙ ለዓይነ ሥውርነት እና ለመስማት ችግር አለፍ ሲልም ለሞት እንደሚዳርግ ገልጸዋል።
‎ለበሽታው በቀጥታ የሚፈውስ መድኃነት ባይኖርም የበሽታውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ቫይታሚን ኤ ጨምሮ ሌሎች የሕክምና እርዳታዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል። ‎መደበኛ ክትባት ያልወሰዱ ሕጻናትን በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡ የክትባት አማራጮች ማስከተብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
‎በሽታው ምልክት ከማሳየቱ በፊት የሚተላለፍ ቢኾንም ምልክቱ የታየባቸውን ሕጸናትን ለይቶ በመንከባከብ እና ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
‎እንደ ክልል በመደበኛ ፕሮግራም በጤና ተቋማት ክትባቱን በመስጠት የመከላከል ሥራው እየተሠራ ነው ብለዋል።
‎በኢንስቲትዩቱ በኩፍኝ የታመሙ ሰዎችን ቅኝት በማድረግ ምርመራ ተወስዶ ይረጋገጣል። በዚህም በአንድ አካባቢ በ28 ቀን ውስጥ ሦስት በላበራቶሪ የተረጋገጠ ወይም አምስት ተጠርጣሪ ካለ ወረርሽኝ ነው ተብሎ የምላሽ ሥራዎች እንደሚሠሩ ነው የገለጹት። የቅኝት፣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ፣ መደበኛ ክትባቱን ማጠናከር እና ወረርሽኝ ሲኖር ምላሽ ሰጭ ክትባት የመስጠት ተግባራትም እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
‎በሽታው ምልክት ሲያሳይ በተለምዶ ልጆችን በቤት ውስጥ ይዞ ቡና በማፍላት ሕክምና እንዳያገኙ ማድረግ ጉዳት ሊያመጣ ስለሚችል ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ኩፍኝ መታየቱን እና በቅርቡ ከተከሰቱት ግን አብዛኞቹ ናሙናዎች የሩቤላ መኾናቸውን ገልጸዋል።
‎ምልክት ያለው ሰው ሲኖር በ6981 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ መሥጠት እና መረጃ ማግኘት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት እየተደረገ ነው።