በአማራ ክልል የጅፕሰም ምርት ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም ኾኗል።

10

 

ባሕርዳር፡ የካቲት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማዕድን የሚባሉት በተፈጥሮ ሂደት በመሬት ላይ ወይም በውስጥ የተፈጠሩ፤ በውኃ ሥር የተፈጠሩ፤ ዋጋ ያላቸው ጠንካራ፣ ፈሳሽ ወይም ጋዝ ነክ ንጥረ ነገሮች ናቸው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለጌጣጌጥ እና ለገንዘብ ምንጭነት የሚያገለግሉ ናቸው። የጅፕሰም ማዕድን ደግሞ ለኮንስትራክሽን ከሚያገለግሉት መካከል አንዱ ነው።

የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበባ ጌታሁን ክልሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኾኑ ከፍተኛ የማዕድን ሃብት ክምችት እንዳለው ተናግረዋል። ይህም በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።

በጥናት ከተረጋገጡ ሃብቶች መካከል ጅፕሰም አንዱ ነው ብለዋል። በዓባይ ሸለቆ አካባቢዎች በስፋት እንደሚገኝም አንስተዋል።

በዋናነት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን፣ እነማይ እና እናርጅ እናውጋ ወረዳዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ደግሞ በመርሐቤቴ እና አካባቢው በስፋት እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት።
አሁን ላይ የክልሉ የጅፕሰም ምርት በሁለት መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደኾነም ገልጸዋል።

ለሲሚንቶ ግብዓት እና እሴት ተጨምሮበት በጅፕሰም መልክ ለገብያ ይቀርባል ነው ያሉት። ማዕድኑ ጠቀሜታው የጎላ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የማዕድን ኢንዱስትሪ ተቋቁሞ ወደ ገበያ እንዲወጣ እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።

በዚህም በምሥራቅ ጎጃም ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን በብዛት በዘርፋ ለተሠማሩ ድርጅቶች ፍቃድ መሰጠቱንም ገልጸዋል።

ፋብሪካዎች ተገንብተው ማዕድኑን እሴት ጨምረው በማምረት ለገብያ እያቀረቡ መኾኑንም ጠቅሰዋል። እንደ አማራ ክልል ማንኛውም ማዕድን እሴት ሳይጨመርበት በጥሬ ምርት ከክልሉ እንደማይወጣም አንስተዋል።

በዚህ ላይም ከፋብሪካዎች ጋር ቅድመ ስምምነት መፈጠሩን ነው የጠቀሱት። ይህን ተላልፎ የሚገኝ አካል ደግሞ ተጠያቂ የሚኾንበት አሠራር እንዳለ ነው ያነሱት።

በአማራ ክልል በጅፕሰም ማዕድን ዘርፍ ፈቃድ ወስደው ከሚሠሩ ድርጅቶች መካከል የየትመን ጅፕሰም እና የጅፕሰም ውጤቶች ማምረቻ እና መሸጫ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አንዱ ነው።

ማኅበሩ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ዓለሙ አደራው በአማራ ክልል ብሎም በኢትዮጵያ የሚታየውን የግንባታ ግብዓቶች እጥረት ለመፍታት ፋብሪካው መቋቋሙን ተናግረዋል።

የጅፕሰም ዱቄት እና ጅፕሰም ቦርድ ሥራዎችን ጥሬ ምርት በስፋት በሚገኝበት ደጀን አካባቢ በሚገኘው የዓባይ ሸለቆ አካባቢ በሁለት ፋብሪካዎች እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የጅፕሰም ጥሬ እቃ ላይ እሴት በመጨመር የተመረቱ ምርቶችን አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በግንባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ድርጅቶቾ እና ግለሰቦች ምርቱን እያቀረበ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አሁን ላይ ጥሩ የሚባል የሥራ እንቅስቃሴ አለን ነው ያሉት። ይህም ከሀገር ውጭ ይመጡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር በቀል ምርቶች በመተካት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ነው ያስገነዘቡት።

ለሥራ ዕድል ፈጠራም አበርክቶው ጉልህ እንደኾነ ነው የገለጹት። ከ360 በላይ ወገኖች በቋሚ እና በጊዚያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር መንገዶች የመዘጋት እና የመከፈት ኹኔታ ስለነበር ምርቱን የሚገዙ ደንበኞች ቁጥር ቀንሶ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትምህርት ተደራሽነት ሽፋንን ከማሳደግ አኳያ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።
Next articleየኢንዱስትሪዎችን የኃይል አቅርቦት ለማሻሻል እየተሠራ ነው።