የዲጂታል ዘላንነት ምንድን ነው?

6

ባሕር ዳር፡ የካቲት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርብ የምናውቀው ዘላንነት የግጦሽ መሬት ፍለጋ የከብት ጭራ ተከትሎ ከሚሄደው ሰው ጋር አያይዘን ነው። በዲጂታል ዓለም ያለው ዘላንነት ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀስን የምንሠራው ከመኾኑ አንጻር መመሳሰል ቢኖረውም የቴክኖሎጂ ዕድገት የፈጠረው አዲስ መልክ ያለው ዘርፍ ነው፡፡

ፍሪደም ኢዝ ኤቭሪ ቲንግ የተሰኘ ድረ ገጽ ዲጂታል ዘላንነትን ለመግለጽ ዲጂታል ዘላኖች ማን ናቸው ከሚለው ጀምሮ ያስረዳል። ቋሚ በኾነ የመኖሪያ ቦታ ሳይወሰኑ የበይነ መረብን በመጠቀም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተዘዋወሩ በርቀት የሚሠሩ ሰዎች ዲጂታል ዘላኖች እንደሚባሉ ይጠቅሳል።

የዚህ ዓይነቱ ዘላንነት የዲጂታል መሠረተ ልማት ከማደጉ እና ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ በርቀት በሚሠሩ ሥራዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተለመደ መጥቷል።

በኢትዮጵያም የዲጂታል መሠረተ ልማት ላይ ባሉ ተስፋ ሰጭ ዕድገቶች እና እየተመቻቹ ባሉ የዲጂታል ሥልጠናዎች አማካይነት እዚህ ኾነው የተለያዩ የዓለም ክፍል ተቀጥረው የሚሠሩ ወጣቶች ተፈጥረዋል፡፡

እነዚህ ወጣቶች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ የሚሠሩ ብቻም ባለመኾናቸው ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ዘላን ላንላቸው እንችላለን፡፡

ዲጂታል ዘላን የሚል መጠሪያ ለመስጠት በርቀት ሥራ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ የሚሠሩ ሊኾኑ ይገባል፡፡

በራሳቸው ጥረት የዲጂታል ዘላንነት እና የርቀት ሥራዎችን የሚሠሩ ወጣቶችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ከአሚኮ ጋር በስልክ ቃለ መጠይቅ ቆይታን ያደረገው ወጣት ቴዎድሮስ አንዱ ነው። ቴዎድሮስ የአውሮፓ እና የአሜሪካን ሀገራትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በመንቀሳቀስ በርቀት ትላልቅ የሶፍትዌር ልማት ፕሮጄክቶች ላይ ይሠራል።

ይህ ወጣት ወደ ዚህ ሥራ የገባው ሊንክድኢን የትስስር ገጽ ላይ አቅሙን እና የሥራ ልምዱን የሚገልጽ ፕሮፋይል በማዘጋጆት መኾኑን ተናግሯል። ወደ ርቀት ሥራው ከመግባቱ በፊት ለአጭር ጊዜ በሶፍትዌር ልማት ተቀጥሮም ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ወጣት ቴዎድሮስ የሪሞት ሥራ በመሥራቱ በሚሳተፍባቸው ትልልቅ ፕሮጄክቶች ከሚያገኘው ትልቅ የቴክኒክ ክህሎት ባሻገር ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚገኝበትም አብራርቷል፡፡

ወደ ዲጂታል ዘላንነት ወይም እየተንቀሳቀሱ የሚሠሩት የርቀት ሥራ ጋር ተያይዞ ነገሮች አልጋ በአልጋ አለመኾናቸውንም ተናግሯል፡፡ የኔትወርክ እና የኀይል መቆራረጥ ችግሮችም ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ አማራጭ ኔትወርክ ማዘጋጃት፣ የኀይል መቆራረጥ የሌለባቸው አካባቢዎች ላይ ኾኖ መሥራት እና ጥሩ የባትሪ አቅም ያላቸውን ላፕቶፖችን መጠቀም አስፈላጊ መኾኑን ተናግሯል፡፡

አሁን ላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በፍጥነት ማደግ ብዙ ሥራዎች እንዲሠሩ ማስቻሉን ይገልጻል። ይሁን እንጅ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በርቀት ተቀጥረው ለመሥራት ትንሽ ፈታኝ ነገር ቢኖረውም ወጣቶች ጥሩ ፕሮፋይል በማዘጋጀት እና በማጋራት ዕድሉን መሞከር አለባቸው ብሏል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎትን አለመጠቀም ጥሩ አይደለም ያለው ወጣት ቴዎድሮስ የምንሠራውን ሥራ ግን በመረዳት ውስጥ ኾነን መፈጸም ይገባል ብሏል።

እኛ ቴክኖሎጂውን ባለመጠቀማችን ከሚጠቀሙ ሰዎች ጋር የሚፈጠረውን ልዩነት ሲያስረዳ “እኛ በብስክሌት ስንሄድ በመኪና እንደሚቀድመን ሰው” ዓይነት ክፍተት ይፈጥርብናል ብሏል። ቁምነገሩ አውቆ መሥራቱ ላይ መኾኑን ገልጿል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግጭት የወለደው የአዕምሮ ቁስለት እና መፍትሄው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጎኖፋ የተቀናጀ የምግብ ኢንዱስትሪ ግንባታን አስጀመሩ።