
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለሰዲ ጫንቃ እና ሃዋ ገላን ወረዳዎች ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣ ያለውን የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትን ለመመልከት እድል አግኝቻለሁ ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለግብርና ሥራ የማይቋረጥ የውኃ አቅርቦትን በሚያረጋግጥ መልኩ የአካባቢውን የተፈጥሮ መልክዓ ምድር በአግባቡ ለመጠቀም ታስቦበት የተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል።
የመስኖ ሥራውን በቀጥታ ጥቅም ላይ በማዋል የታረሰ እና የለማ መሬት ለኅብረተሰቡ ጉልህ ፋይዳ ማስገኘት መጀመሩም አበረታች ነው ብለዋል።
አብሮ የተሠራው የመንገድ መሠረተ ልማትም የገበያ ተደራሽነትን አስፍቷል፣ የነዋሪዎችን የቀን ተቀን ኑሮ እንቅስቃሴንም አቅልሏል ነው ያሉት።
አካባቢው ሰፊ የግብርና እምቅ አቅም ያለው እንደመኾኑ እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ እና ብርቱካን ያሉትን ምርቶች በመደገፍ ረገድ የመስኖ እና የመሠረተ ልማት ሥራ ዘላቂ የገጠር ግብርና ልማትን ማሳደግ እንደሚችል አብነት ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
