
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የምሥራቅ እዝ ከፍተኛ የሠራዊት መሪዎች እና የክልል እና የዞን የጸጥታ መሪዎች በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ በባሕርዳር ከተማ መክረዋል፡፡
የምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ ኢትዮጵያን ውጊያ ቢገጥሙ ማሸነፍ እንደማይችሉ የተረዱት ጠላቶቻችን ግንባር ፈጥረው የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን፣ ያኮረፉ ኀይሎችን በማሠልጠን፣ በማደራጀት እና የተለያዩ መደለያ ጥቅማ ጥቅሞችን በመስጠት እርስ በርሳችን በማጋጨት ኢትዮጵያን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረት አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡
በጸጥታ ግብረ ኀይሉ እቅድ መሠረት ባደረግነው የተቀናጀ ስምሪት በጽንፈኛው ላይ ከፍተኛ ምቶችን አሳርፈንበታል ነው ያሉት ፡፡ ጽንፈኛው የተኩስ አቅሙን ተነጥቋል፤ የሎጂስቲክስ ድጋፉን አድርቀነዋል ብለዋል።
ሴሎቹ እንደተያዙበትም ገልጸዋል። በየቀጣናው የሸመቁ የጠላት መሪዎች መምራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመኾናቸው አባሉ እየተበተነ ራሱን ለማትረፍ እየጣረ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ለሠራዊቱ እጅ እየሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል።
በቅርቡ የተሰሩት የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች የጠላትን ገመና ያጋለጡ ፣ የጠላትን ትጥቅ ያስፈቱ ፣ ጽንፈኛው እስርስ በርሱ እንዳይተማመን ያስቻሉ እና ከሕዝብ የነጠሉት ናቸው ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ እና የጸጥታ መዋቅር እያደረገ ያለው ተጋድሎ የሚደነቅ መኾኑንም ገልጸዋል። የክልሉ የጸጥታ ኀይል ብቻውንም ኾነ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ተጣምሮ ያደረጋቸው ስምሪቶች ውጤታማ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ የበለጠ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ፣ ሠራዊቱ ቀጣይ በሚሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ፣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
በቀጣይ መፈጸም አላባቸው በተባሉ ጉዳዮች ላይም አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ ( ዶ.ር) መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይል ጠላትን በመደምሰስ ክልሉ ከተጋረጠበት አደጋ በመታደግ ወደ ልማት እንዲዞር ማድረጉን ገልጸዋል።
ከምሥራቅ እዝ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በቀጣይም ሕዝቡ እና የጸጥታ ኀይሉ የተበታተነውን ተላላኪ ጽንፈኛ መድረሻ አሳጥቶ መደምሰስ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
