ብሔራዊ ጥቅምን እና አቅምን ያስቀደመ መስተንግዶ

13
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከሐረር እስከ ኢስታምቡል፤ ከአንካራ እስከ አዲስ አበባ ዘመን ተሻጋሪ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል፤ ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ፡፡
ጥንታዊነት፣ ሥር የሰደደ የዲፕሎማሲ ጥረት እና ብዝኀ ማንነት የሚያመሳስላቸው ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይመዘዛል፡፡
ኦቶማን ኢምፓየር በቀይ ባሕር ላይ ለመጠቀም ፍላጎቱን ሲያሰፋ የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በዘመን መካከል ዘምኖ ቱርክዬ ከሰሀራ በርሐ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል የመጀመሪውን ኢምባሲዋን የከፈተችው በኢትዮጵያ ነበር፡፡
በመከባበር ላይ የተመሠረተው የሁለቱ ሀገራት የእርስ በእርስ ግንኙነት በንግድ፣ በባሕል፣ በፖለቲካ፣ በትምህርት እና መሰል ግንኙነቶች ታግዞ ወደ ዘላቂ እና ተግባራዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተሸጋግሯል።
አሁን ላይ ደግሞ “የአመራር ዲፕሎማሲ አቅኝ” የሚል መጠሪያ የተቸራቸው የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጠይፕ ኤርዶዋን ሀገራቸውንም ወደ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነት አሸጋግረዋታል፡፡ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ቀደምት ግንኙነት በማጠናከር ለቀይ ባሕር ቀጣና ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ሁለቱ ሀገራት አብረው እንዲሠሩ ሌላ ምዕራፍ የከፈተ ይመስላል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ጂኦ-ፖለቲካዊ ተፅዕኖዋ እየጨመረ የመጣችው ቱርክዬ ግጭትን አስቆሞ ሰላምን በማምጣት በኩል ተጠቃሽ አሸማጋይ እስከ መኾን ደርሳለች፡፡ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን፣ ዩክሬን እና ሩሲያን፣ ታሊባን እና ፓኪስታንን በማሸማገል በበጎ የምትነሳው ቱርክዬ ዓለም አቀፍ መረጋጋትን በማምጣት በኩል ተጠቃሽ ሀገርም ኾናለች፡፡
በተለይም ቱርክዬ ከቀጥተኛ ጫና እና ተፅዕኖ በተላቀቀ እና የተሸማጋይ ሀገራትን ይሁንታ ባገኘ መልኩ የምታደርገው አስታራቂነት ለዘላቂ ሰላም ተተግባሪነት አርዓያ ተደርጎ ይነሳል፡፡
ታዲያ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ግብዣ ምድረ ቀደምቷን ሀገር ኢትዮጵያን የጎበኙት እና ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ፕሬዝዳንት ረጅብ ጠይፕ ኤርዶዋን የኢትዮጵያን ወቅታዊ እና ቀዳሚ የባሕር በር ጥያቄ እንዴት ይመለከቱታል የሚለው ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ሁለቱ መሪዎች ቆይታቸውን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የቀይ ባሕሪን ጉዳይ አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ ዝግ ኾና መቀጠል እንደለለባት በተለመደው መልኩ ጠንካራ አቋማቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገር ቱርክዬ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንድትፈጥር ጠይቀዋል፡፡
ዛሬም ሰላማዊ አማራጮችን እንደ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ አጥብቃ የምትከተለው ኢትዮጵያ በትናንቱ የመሪዎች መግለጫ ላይም ብሔራዊ ጥቅምን እና ሀገራዊ ደኅንነትን ባስቀደመ መልኩ የይገባኛል ተፈጥሯዊ ጥያቄዋን በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል አሰምታለች፡፡
ፕሬዝዳንት ረጅብ ጠይፕ ኤርዶዋንም የኢትዮጵያ አርዓያነት ያለው አሥተዳደር ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያለውን ላቅ ያለ ሚና ጠቁመዋል። ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ሁለንተናዊ መሻት እና ፍላጎት ጎን እንደምትቆም አረጋግጠዋል፡፡
የዓለም ዐይኖች ወደ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና እያማተሩ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣናው ያለውን የኀይል እና የፍላጎት አሰላለፍ ፍፁም ጤናማ አድርጎ ለማዝለቅ የኢትዮጵያ ድርሻ የላቀ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያም በዚህ ጉብኝት ስኬታማ ግብዣ እና መስተንግዶዋን ለዓለም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ከማሳየት ባለፈ ብሔራዊ ጥቅሞቿን እና አቅሞቿን አሳይታበታለች፡፡ ሰላምን አጥብቃ የምትሻ፣ ፍላጎቶቿን በግልጽ የለየች እና ለፍላጎቶቿ መሳካት ከግማሽ ርቀት በላይ የምትጓዝ ሀገር መኾኗንም አሳይታለች።
በታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleዘመን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ወዳጅነት!
Next articleየወርቄ – ያያሁሞ – አራቱ ጋሪያ የመንገድ ግንባታ ሥራ ተጀምሯል።