
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክቱን ይፋ የማድረግ ክልል አቀፍ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ራዕይ እና ፍላጎታችን ነው ብለዋል። ፓርቲው ብዝኀነትን የሚያከብር እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ትልቅ ዋጋ ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
ብልጽግና በጥልቀት የሚመለከት እና አድርጎ የሚያሳይ፣ ኢትዮጵያ ኋላቀርነትን፣ ድህነትን፣ ግጭትን እና ጦርነትን ተሻግራ ከፍ ብላ እንድትታይ ሕዝብን በፍትሐዊነት እያገለገለ የሚገኝ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ያለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ ትልቁ ጥማት ዴሞክራሲ ነበር ያሉት አቶ ይርጋ ቋሚ እና የጸና የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲኖር ብልጽግና አልሞ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። የፉክክር እና የትብብር ዴሞክራሲን በሚዛናዊነት የሚከተል ፓርቲ መኾኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ መነሻ አቅሞች እና ሃብቶች አሏት፣ ብልጽግናም ትላልቅ ትልሞችን ይዞ ለሀገር ከፍታ በመሥራት ላይ ነው ብለዋል። ሰብዓዊ ልዕልናን፣ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እና የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር መፍጠርን አልሞ እየሠራ የሚገኝ የሃሳብ ፓርቲ እንደኾነም ተናግረዋል።
“ብልጽግና የሚኾነውን የሚናገር፣ የተናገረውንም የሚያደርግ የተግባር ፓርቲ ነው” ብለዋል። መከፋፈልን ሳይኾን አንድነትን አጥብቆ የያዘ፣ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚበጅ ሕግን ለማስከበር እና ፍትሕን ለማስፈንም እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የፍትሕ ተቋማት የማሻሻያ ሥራዎች ተከናውነዋል፣ የገጠሙ የሰላም ችግሮችም በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ እልባት እንዲያገኙ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ አህጉራዊ ተደማጭነቷ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ከፍ ብሏል፤ ይህም የፓርቲውን የዲፕሎማሲ ስኬት ተግባራዊ ማሳያ መኾኑን ነው ያነሱት።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲ ምልክት የስንዴ ነዶ መኾኑንም ጠቁመዋል። ስንዴ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጫ ነው፣ ነዶውም የአንድነት እና የመተባበር ምልክት ነው ብለዋል።
አማራ ክልል ለዴሞክራሲ እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ እርሾ እና እሴት ያለው፣ ለሰላም እና ለልማት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ለምርጫም ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ክልል እንደኾነ ጠቁመዋል።
መጭው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ችግሮች የሚታረሙበት፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና ነጻ እንዲኾንም በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
