
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክቱን ይፋ የማድረግ ክልል አቀፍ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መጭው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና የሕዝብ ድምጽ የሚከበርበት እንዲኾን ብልጽግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እየሠራ ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ችግር የገጠማትን ሀገር ያዳነ እና አንድነት እንዲሰፍን እየሠራ የሚገኝ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። ኅብረ ብሔራዊነትን፣ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት፤ ድህነት እና ኋላቀርነትን፣ ግጭት እና ጦርነትን ለማስቀረት፤ ጸረ ዴሞክራሲ የኾነ ሥነ ምኅዳርን በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ለመተካት እየሠራ ያለ ፓርቲ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የእዳ ጫና ከትልቅነቷ እንድታፈገፍግ ያስገደዳትን ኢትዮጵያ እዳዋን ያቃለላት እና ወደ ቀደመ ገናናነቷ ተመልሳ ተምሳሌት ሀገር እንድትኾን ያስቻላት ፓርቲ ብልጽግና ስለመኾኑም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በሯ ተዘግቶ ከዓለም ተገልላ ቆይታለች፤ ይህንን ጉዳይም በግልጽ በመሞገት ሀገሪቱን የባሕር በር ባለቤትነት በዓለም አደባባይ የጠየቀ እና ለተግባራዊነቱም በትጋት እየሠራ የሚገኝ ፓርቲ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
ፓርቲው በርካታ ተጨባጭ ለውጦችን ያስመዘገበ እና የትናንት ችግሮችን ማረም ብቻ ሳይኾን የነገንም መዳረሻ አቅዶ እየሠራ ያለ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ከድህነት በመውጣት ዓለም በእድገቷ የሚያውቃት ሀገር ለመገንባት ርዕይ በመያዝ እና ለርዕይም በመታመን እየተሠራ ነው ብለዋል።
መጭው ምርጫ በሕዝብ ዘንድ ፍጹም ተዓማኒ እና ፍትሐዊ እንዲኾን ከወዲሁ እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ሕዝብ በምርጫ ተማምኖ ተሳታፊ ሲኾን የዴሞክራሲ ባሕል ይጎለብታል፤ ሰላምም ይሰፍናል ነው ያሉት።
ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ በመሳብ ተኪ ምርቶችን ማምረት፣ ድህነትን መቀነስ እና ሀገርን ወደ ተወዳዳሪነት ጎራ ማሰለፍ ስለመቻሉም ጠቁመዋል።
በተፈጥሮ እና በሰው መካከል በነበረው የተዛባ መስተጋብር ምክንያት ሀገራችን ለተደጋጋሚ ድርቅ እና ጉስቁልና ስትጋለጥ ቆይታለች ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ብልጽግና ፓርቲ ይህንን ለማረም የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄን ፈጥሮ ሰው እና ተፈጥሮን የሚያስታርቁ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
