ለቀይ ሽንኩርት ምርት የገበያ ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል።

14
ባሕር ዳር: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የቀይ ሽንኩርት በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አንዱ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነው።
አርሶ አደር ብዙነህ አሰፋ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጠገዴ ወረዳ የዳንሻ ዙሪያ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው። በ17 ሄክታር መሬት ላይ ቀይ ሽንኩርትን በመስኖ እያለሙ እንደሚገኙ ከአሚኮ ዲጂታል ሚድያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ለ5 ተከታታይ ዓመታት ቀይ ሽንኩርትን በማልማት ውጤታማ እንደኾኑም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት 2 ሺህ ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ያነሱት አርሶ አደሩ ከ800 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በዚህ የመስኖ ወቅትም 3 ሺህ ኩንታል የቀይ ሽንኩርት ምርት ለማግኘት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
“የገበሬን ምርት ደላላ እየተጠቀመበት ነው” ያሉት አርሶ አደር ብዙነህ የገበያ ትስስር ባለመኖሩ ምርታቸውን በቅናሽ ዋጋ እየሸጡ መኾኑን ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት አንድ ኪሎ ሽንኩርት 20 ብር ተሽጦ ነበር፤ ዘንድሮ ግን አንድ ኪሎ 10 ብር እየተሸጠ መኾኑንም ነው የተናገሩት። የገቢያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውም ጠይቀዋል።
በዞኑ ከ7 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን የተናገሩት ደግሞ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ እንዳልካቸው አስፋ ናቸው።
በቀይ ሽንኩርት ከ2 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት ታቅዶ 3 ሺህ 85 ሄክታር መሬት ለምቷል ብለዋል። 688 ሺህ 790 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ከ5 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ እንደኾኑም አንስተዋል።
የገቢያ ትስስር ለመፍጠር የለማውን እና የሚጠበቀውን ምርት በማሳወቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የሰብል እና ኢንዱስትሪ ምርቶች ግብይት ዳይሬክተር ልንገረው ሀበሻ አምራችን መሠረት ያደረገ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ወቅታዊ መኾኑንም አንስተዋል። የቀይ ሽንኩርት ምርትን ጅምላ ነጋዴዎች ወደ አርሶ አደሮች ማሳ ገብተው ምርት እንዲገዙ፤ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቶች እንዲገበያዩ አማራጭ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ነው የገለጹት።
በከተሞች ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር በመሠራቱ ውጤት መምጣቱንም ገልጸዋል። ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን የመቆጣጠር ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች አካባቢ የሚገኙ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር አርሶ አደሮች ከቀበሌ ባለሙያዎች ጋር በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች በአካባቢው ለሚገኙ ዞኖች እና ከተሞች የቀይ ሽንኩርት ምርታቸውን እንዲያቀርቡ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የሰላም እጦት መኖር ምርቶችን አጓጉዞ ለመሸጥ እንቅፋት መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
የግብርና ምርቶች በነጻነት ከቦታ ቦታ ለገበያ እንዲቀርቡ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article183 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ባለሀብቶችን መቀበሉን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየአፈጣጠር ችግር ላለባቸው ወገኖች የሕክምና ዘመቻ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ተካሂዷል።