183 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ባለሀብቶችን መቀበሉን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

20
‎ባሕር ዳር: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸሙን እየገመገሙ ነው።
‎
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በበጀት ዓመቱ በክልሉ አሻጋሪ ዕቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ አምራች ኢንዱስትሪው ነው ብለዋል።
‎
‎በበጀት ዓመቱ 609 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ነዋይ ወደ ክልሉ ለማምጣት ታቅዶ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። ባለፉት ስድስት ወራት በተቋሙ የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል ነው ያሉት።
‎ በአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ በማዕድን፣ በአገልግሎት፣ በዘመናዊ ግብርና እና በቱሪዝም የተሻሉ አልሚዎችን ለማምጣት ታቅዶ ተሠርቷል ብለዋል።
በዚህም 183 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 1 ሺህ 867 አዳዲስ አልሚ ባለሀብቶችን መቀበላቸውን ገልጸዋል። ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም በክልሉ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መኾኑን ነው የተናገሩት።
‎
‎በስድስት ወራት 85 አምራች ኢንዱስትሪዎች እና 280 ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ወደ ምርት ገብተዋል ነው ያሉት።
‎
‎በመሬት አቅርቦት በኩል የነበሩ ችግሮችን ከመሬት ቢሮ ጋር በመፍታት ለ177 አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ለ122 ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች 4 ሺህ 126 ሄክታር መሬት ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
‎
‎በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገቡ ከ321 ቶን በላይ ተኪ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማምረት ከ366 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል ነው ያሉት። ‎43ሺህ ቶን የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ 112 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንደተገኘም ገልጸዋል።
‎የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 62 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል።
‎
‎ከ47 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን እና የዘርፉን አገልግሎት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደኾነም አንስተዋል። ወደፊትም ችግሮችን መፍታት እና ተቋማዊ ቅንጅት ላይ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
‎
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመግባባት የተሳነው ትውልድ ሀገራዊ ነጻነቱን እና ደኅንነቱን ማስጠበቅ አይችልም።
Next articleለቀይ ሽንኩርት ምርት የገበያ ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል።