
ባሕር ዳር: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የ”ዌስትፋሊያ” የሰላም ሥምምነትን ተከትሎ እንደተመሠረተ ይነገራል።
ሥምምነቱ በአውሮፓ የተከሰተውን የረዥም ጊዜ የሃይማኖት ጦርነት አስቁሞ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት መጀመሩን ያመለከተ ነው።
ሥርዓቱ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ከፈረንሳይ አብዮት ጀምሮ ይበልጥ ተጠናከረ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የብሔራዊነት ንቅናቄዎች በአውሮፓ ይበልጥ ተስፋፉ፤ እንደ ጀርመን እና ጣሊያን የመሳሰሉ ሀገሮች መዋሀድን ተከትሎ የዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ቅርጽ ይበልጥ እየተጠናከረ፣ ከአውሮፓ ባለፈ ወደ ሌሎች ክፍለ ዓለማትም እየተስፋፋ የመጣበት ወቅት እንደኾነ ይነሳል።
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የመጀመሪያውን መሠረት ያገኘው ደግሞ በ1855 ዓ.ም የአጼ ቴዎድሮስ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ እንደኾነ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።
አጼ ቴዎድሮስ በ1855 ዓ.ም ወደ ንግሥና ሲመጡ በ”ዘመነ መሳፍንት” የተበታተነውን ሀገር የማሠባሠብ ጥረት ጀመሩ። ይህም ሂደት የዘመናዊ መንግሥት መሠረት የኾነውን ማዕከላዊ ሥልጣን ለማጠናከር የመጀመሪያ እርምጃ ነበር። ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ የመጡት ነገሥታትም ይህንን ሂደት ይበልጥ እንዳጠናከሩት ነው የሚነገረው።
በእንጀባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህር ዓለምነህ አጋዤ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እ.አ.አ በ1648 የዌስት ፋሊያን ሥምምነት ተከትሎ በአውሮፓ ተጀምሮ በሂደት ወደ ሌሎች ሀገራት እየሰፋ እየሰፋ መሄዱን ገልጸዋል።
ሀገራት የተጠናከረ ሀገረ መንግሥት ከመሠረቱባቸው መንገዶች ውስጥ ደግሞ ብሔራዊ መግባባት ዋነኛው መንገድ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ለመኾኑ ብሔራዊ መግባባት ምንድን ነው?
መምህሩ እንዳሉት ብሔራዊ መግባባት አንድ ወጥ ብያኔ ባይኖረውም በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ስለወደፊቱ የሀገር እጣ ፋንታ በጋራ የሚወስኑበት፣ ለአንድ ሀገር ብሔራዊ ጥቅም እና ፍላጎት በጋራ የሚቆሙበት መንገድ ነው።
ብሔራዊ መግባባት በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖቶች እና የፖለቲካ ዕይታ ያላቸው ሰዎች በመነጋገር እና በመግባባት ላይ ተመስርተው በአንድነት የሚኖሩበት መንገድ ነው። ብሔራዊ መግባባት ልዩነትን በማክበር በአንድ ሀገር ውስጥ በሰላም በጋራ መኖር ነው።
ሰላምን እና ፍትሕን ማስቀደም፣ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መኾናቸውን መቀበል፣ ልዩነቶችን እንደ ችግር ሳይኾን እንደ ሃብት መመልከት፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት ነው።
መምህሩ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለዘመናት አንድነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር ብትኾንም ባለፉት ዓመታት በዋልታ ረገጥ የፖለቲካ ፍላጎት እየተፈተነች ትገኛለች።
በሀገሪቱ የተከሰቱ አለመግባባቶች እና ግጭቶች በተገቢው መንገድ ካልተያዙ እና ካልተገሩ የሀገረ መንግሥቱን ሕልውና ሊፈታተኑ ወደ ሚችልበት ደረጃ ሊደርሱ እንደሚችሉ ነው የገለጹት።
እነዚህ ለሀገረ መንግሥት ፈተና እየኾኑ የመጡ ችግሮችን በመለየት መፍታት እና ብሔራዊ መግባባት ላይ የሚያደርሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።
በተለይም ደግሞ የሀገር ምልክት በኾኑ እንደ ሰንደቅ ዓላማ፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ የዓድዋ ድል በመሳሰሉ አሠባሣቢ የጋራ ትርክቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል።
እነዚህን የሀገር ምልክቶች በዓመት አንድ ጊዜ ተሠባሥቦ ከማክበር ባለፈ በሥርዓተ ትምህርት በማካተት በተደራጀ መንገድ በትምህርት መልክ መስጠት እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ከዚህም ባለፈ በሚዲያ እና ሌሎች አማራጮች ለማኅበረሰቡ ማስገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። እንደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመሳሰሉ የሀገሪቱን የጋራ ራዕይ የሚወስኑ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሠጥት መሥራት ያስፈልጋል።
መግባባት የተሳነው ትውልድ ሀገራዊ ነጻነቱን እና ደኅንነቱን ማስጠበቅ እንደማይችል ያነሱት መምህሩ የፖለቲካ ጠያቄ አለኝ የሚል ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ኾነ ቡድን ሥልጣንን እና ግላዊ ፍላጎቱን ከማስቀደም ይልቅ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለጋራ ራዕይ፣ ለሀገረ መንግሥት ቀጣይነት እና ለሀገር ሕልውና ቅደሚያ ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል።
ምሁራን አርስ በእርስ ከመሳሳብ ይልቅ ዕውቀታቸውን ለሀገረ መንግሥት ግንባታም ሊያውሉ ይገባል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የታሪክ እና የሥርዓት ግጭቶችን ሁሉንም ባሳተፈ መንገድ በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ ዕድሉን ማመቻቸት ይገባዋልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
