“ግብር የዜጎች አርበኝነት የሚገለጽበት ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

2

ባሕር ዳር፡ የካቲት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከገቢዎች ሚኒስቴር ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የዕውቅና እና የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ግብር እና የግብር ስርጭትን ማዘመን ለአንድ ሀገር ሥርዓተ መንግሥት መቀጠል እና መጽናት ቁልፍ ከኾኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ግብር የዜጎች አርበኝነት የሚገለጽበት መኾኑን ተናግረዋል። ገቢ ካልተሰበሰበ እና ዜጎችም ግዴታቸውን ካልተወጡ ሀገር ለተመጽዋችነት ትዳረጋለች ብለዋል። በዚህም ምክንያት የሀገር ክብር ዝቅ ይላል ነው ያሉት።

ግብር የዘመናዊ እና የዳበረ የመንግሥት ሥርዓት መገለጫ መኾኑንም ገልጸዋል። የግብር ሥርዓቱን መቆጣጠር እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የመንግሥት መገለጫ መኾኑን ተናግረዋል።

የግብር ሥርዓት መረጋገጥ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ትልቅ አቅም መኾኑን ገልጸዋል። የግብር ሥርዓትን ማዘመን የሀገርን ብልጽግና ማረጋገጥ ነው ብለዋል። የግብር አቅም ሲያድግ መሠረተ ልማት ይሟላላል፤ ዜጎች ተጠቃሚ ይኾናሉ ነው ያሉት። የማኅበረሰብ ዘርፍ ትምህርት እና ጤና ውጤታማ ሥራ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

ዜጎች ታክመው እንዲድኑ፣ የነገ ሀገር ተረካቢዎች በተመቸ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ ግድ እንደሚል ተናግረዋል። ግብር የሀገር ዋልታ እና ማገር መኾኑንም ገልጸዋል።

አማራ ክልል በአቅሙ እና በሚጠበቅበት ልክ ግብር እንዲሰበሰብ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። የእስካሁኑ የገቢ አሰባሰቡ በሚጠበቀው ልክ እንዳልኾነ ነው የገለጹት። ዝቅተኛ የገቢ አሰባሰብ ካለን ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት ይኖራል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል መንግሥት የገቢ አሰባሰብን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ገቢ እናሳድግ ስንል የግብር ጫና እናድርግ ሳይኾን ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ፣ ማዘመን እና ግንዛቤን ማሳደግ ማለት ነው ብለዋል። ግብርን እናሳድግ ሲባል ታማኝ ግብር ከፋዮችን እናሳድግ ማለታችን ነው፤ ግብርን በውጤታማነት እንሰብስብ ማለታችን ነው ብለዋል።

ታማኝ ግብር ከፋዮችን እናበረታታለን፤ ሕገ ወጥ የግብር ሥራን እና ኮንትሮባንድን እንከላከላለን፤ የሕግ ተጠያቂነትን እናረጋግጣለን ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት ግብርን እናሳድግ ሲል የሕዝብን ብልጽግና የማረጋገጥ ግዴታ ስላለበት ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ግዴታችሁን በአግባቡ ስለተወጣችሁ እና ታማኝ ስለኾናችሁ እናመሰግናለን ነው ያሉት። እናንተን ያመሰገነው ግብርን ላለመክፈል የሚደበቁ ባሉበት ሁኔታ በታማኝነት ስለከፈላችሁ ነው ብለዋል። ሌሎችም በታማኝነት ግብርን እንዲከፍሉ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጣሊያን ከአፍሪካ ጋር መተባበር እንጅ መርዳት አትፈልግም” የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሚሎኒ
Next article“አፍሪካ የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን ብቃት ላይ ነች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)