‎የተወዳዳሪ ፓርቲዎች የዕጩዎች ምዝገባ መራዘሙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡

4
ባሕር ዳር: የካቲት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ምርጫ ሥራዎች እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኀይሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
‎ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች የዕጩዎች ምዝገባ ከጥር 1/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ፓርቲዎች የዲጂታል ምዝገባ ሥራው አዲስ መኾኑ እና ጊዜው በማጠሩ ምክንያት እንዲራዘምላቸው በመጠየቃቸው የዕጩዎች ምዝገባ ለ15 ቀናት ተራዝሞ የካቲት 1/2018 ዓ.ም ይጠናቀቅ የነበረው ወደ የካቲት 16 ተዛውሯል ብለዋል፡፡
የዕጩዎች ምዝገባም በዲጂታል አሠራር በጥሩ ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑንም በመግለጫቸው አንስተዋል።
‎ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተገናኘ ቦርዱ የተለያዩ የምክክር መድረኮችን ማካሔዱንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለሚያገኙት የነጻ የአየር ሰዓት ጊዜ ድልድል መመሪያ በቦርዱ ተዘጋጅቶ ለፓርቲዎች ቀርቦ ግብዓት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
መንግሥት የሚመድበውን የበጀት አከፋፈል በተመለከተ ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት መመሪያው እንዲሻሻል ስለመደረጉም አንስተዋል፡፡
‎የፖለቲካ አስቻይ ሁኔታ የለም በሚል ከፓርቲዎች የሚነሳው ጥያቄን በተመለከተ ቦርዱ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ባሉበት ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ለዚህ ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ሁሉም ኀላፊነት እንዳለበት ሁሉም በትጋት ሥራዎችን ማከናወን ለውጤቱ ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
‎ፓርቲዎች ተመዝግበው ከጨረሱ በኋላ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ብቻ ክርክር የሚያደርጉበት፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መርሐ ግብራቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ መዘጋጀት ስላለበት መድረኩን ለማዘጋጀት ቦርዱ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
‎የዕጩዎች ምዝገባ ተጠናቅቆ ለሕዝብ ትችት ከቀረበ በኋላ ፕሮግራማቸውን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሚዲያዎችን ተጠቅመው ክርክር የሚያደርጉበትን ሂደት ቦርዱ ያመቻቻል ብለዋል፡፡
‎የጸጥታ ጉዳይን በተመለከት ቦርዱ ምርጫዎችን ማስፈጸም የሚቻልባቸውን ቦታዎች ለመለየት ከክልል መንግሥታት እና ከጸጥታ አካላት የሚገኙ መረጃዎች ተሰብስበዋል ነው ያሉት፡፡
ቦርዱ በዚህ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት አድርጓልም ብለዋል፡፡
‎ለምርጫ ታዛቢዎች የምዝገባ ሥርዓት መዘርጋቱን እና የምርጫ ሂደቱን ለማሳለጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጅ ውጤቶችን ተግባራዊ እየተደረገ እየተደረገ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
‎ከውጭ ሀገር የሚመጡ ዓለማቀፋዊ ታዛቢዎችን በተመለከተ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ቦርዱ በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
‎የቦርዱን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከ14 ወደ 22 ከፍ ብሏል ነው ያሉት ሰብሳቢዋ፡፡
‎በቀሪ 109 ቀናት ቦርዱ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ ኾኖ እንዲከናወን ጥረቱን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሁሉንም ሱዳናውያን አካታች የኾነ የመፍትሔ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ገለጹ።
Next articleየአፍሪካ የጋራ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት እያደረገች ነው።