
ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ48ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ሥብሠባ እና በ39ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ።
ዛሬ ንጋት አዲስ አበባ ከገቡት መካከል የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩድዘቶ አብላካዋ፣ የሲሸልስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባሪ ፏር፣ የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቸኪህ ናንግ እና የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ሞንደየሰ ሳሚያ ኩምቢያ ይገኙበታል።
በተጨማሪም የኢስዋትኒ የውጭ ጉዳይ እና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ፎሊል ድላሚኒ ሻካንቱ፣ የቶጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሮበርት ዱሰይ፣ የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የምሥራቅ አፍሪካ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ማሕመድ ታቢት ካምቦ እና የላይቤሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳራ በይሶሎው ኒያንቲ አዲስ አበባ ገብተዋል።
እንዲሁም የኮንጎ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኖይላ ናክዊፓኔ አዬጋናጋቶ በ48ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ሥብሠባ እና በ39ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከገቡት መከካል ይገኙበታል።
ሚኒስትሮቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሚኒስትሮች የሥራ አሥፈጻሚ ምክር ቤት ሥብሠባ ለ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
