ሀገርን በማረጋጋት ረገድ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን ሚና ከፍተኛ ነው።

6
አዲስ አበባ: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልከቶ በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።
ውይይቱም በምርጫው ላይ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን ሚና የሚል ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ምርጫ ዕድሜያቸው ለሚጋብዛቸው ዜጎች ሁሉ እኩል ዕድል የሚሰጥ የዴሞክራሲ ትሩፋት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የዜጎች ተሳትፎ የሥርዓቱ መገለጫ ብቻ ሳይኾን ለፍትሐዊ ውክልና እና ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ምሰሶ ኾኖ ያገለግላል ነው ያሉት።
በዚህ ረገድ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ለችግር ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርጉት የተቀናጀ ተሳትፎ ለሥርዓቱ ፍትሐዊነት መሠረት መኾኑንም ገልጸዋል ።
በተለይም ሴቶች ከሀገራችን የሕዝብ ቁጥር አንጻር ግማሽ ያህሉን በመሸፈናቸው እንደ ጤና እና ትምህርት ያሉ መሠረታዊ አጀንዳዎች ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ የሥርዓቱን ቅቡልነት እንደሚያረጋግጡ ነው የተናገሩት።
ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንን እና በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በምርጫ ማሳተፍ ለሀገራዊ መረጋጋት እና ለፖሊሲዎች ተቀባይነት ሚናቸው ከፍተኛ እንደኾነም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ እኒህ አካላት ድምጻቸውን በነጻነት በመስጠት የመንግሥት የሥልጣን ምንጭ እንዲኾኑ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
በምርጫ ወቅት እና በድኅረ ምርጫ ሂደቶች ያላቸውን ሚናም ተገንዝበው ተገቢውን ኀላፊነት እንዲወጡ ማገዝ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሚዲያ አካላትም ተገቢውን ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ በትብብር መሥራት ይጠይቀናል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዮች ስቀው አገልግሎት የሚያገኙበት ተቋም ነው።
Next articleከ170 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጄክቶች ተጠናቅቀው ተመረቁ።