በ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው የዶክተርስ አሊያንስ ጄኔራል ሆስፒታል ተመረቀ።

4
አዲስ አበባ፡ ጥር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዶክተር አሕመድ ረጃ እና ባለቤታቸው ዶክተር ኤልሳቤት ሃሳብ ጠንሳሽነት በ32 ሐኪሞች ጥምረት የተመሠረተው የዶክተርስ አሊያንስ ጄኔራል ሆስፒታል ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።
ለግንባታ እና ለሕክምና ቁሳቁስ ግዥ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ይህ ሆስፒታል 100 የሕሙማን አልጋዎችን የያዘ ሲኾን በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ300 በላይ እንደሚያደርስ ተገልጿል።
የሆስፒታሉ የቦርድ ዳይሬክተር ፕሬዝዳንት ዶክተር አሕመድ ረጃ እንደተናገሩት ተቋሙ ቅንነት እና ርህራሄ የተሞላበት አገልግሎት ለመስጠት በዘመናዊ መሣሪያዎች ተደራጅቷል።
ሆስፒታሉ ዜጎች ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱበትን አስፈላጊነት በመቀነስ በሀገራቸው ጥራት ያለው ሕክምና እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በ2030 ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ለያዘችው ግብ የሆስፒታሉ መከፈት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በተለይም ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን ለመከላከል እና የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት ተቋሙ ከፍተኛ ኀላፊነት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ሆስፒታሉ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ በባለሙያዎች ሥልጠና እና የሀገሪቱን የጤና ፖሊሲ በመደገፍ ረገድ በትኩረት እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ሐይቅ የመጣ ሰው ታሪክ ሳይማር፣ ፍቅር ሳይጎነጭ፣ ደስታ እና ሰላምን ሳይከናነብ ወደ መጠባት አይመለስም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበትምህርት ላይ የደረሰውን ስብራት ለመጠገን በቁጭት መሥራት ይገባል።