
ባሕር ዳር: ጥር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በመረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ሥፍራ የተገኛችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ታሪክ ጠገብ፣ ፍቅር አዘል፣ ሥራ ወዳድ፣ ሁሉን አቃፊ፣ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ወደ ኾነው ወሎ እንኳን በሰላም መጣችሁ ነው ያሉት።
ገበታ ለትውልድ ለትውልድ የሚጣል አሻራ ነው ብለዋል። የሐይቅ ሪዞርት ዛሬ ላለነው ለእኛ ምንም አይደለም፤ ነገ ሐይቅ ስትለወጥ፣ ትውልድ ሲነሳ ብልጽግናን ሲጎናጸፍ ይህንን ሐውልት እንደ መነሻ ነጥብ ያስታውሰዋል ነው ያሉት።
ጎርጎራ በጣና ሐይቅ ታሪክ ጠገብ አብያተክርስቲያናት፣ ገዳማት፣ መጻሕፍት ያሉበት ከባቢ ነው፤ ያንን አካባቢ ገልጦ ለማሳየት ጎርጎራ ጠቃሚ ነበር፤ ሐይቅም አስደማሚ ታሪክ በግልጽ የሚታይበት አካባቢ ነው ብለዋል።
ያን ታሪክ ለመግለጥ የሚያስችል መሠረተ ልማት ያስፈልግ እንደነበር አንስተዋል። ሐይቅ በ10ኛው ክፍለ ዘመን አርመኖች በገጠማቸው ውጊያ ሀገር ለቀው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ያረፉበት ነው፤ የመኖች በሀገራቸው መኖር ሲሳናቸው መጥተው ያረፉት በሐይቅ ነበር፤ የአውሮፓ አሳሾች የጻፉለት አካባቢ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ፍቅር እና ሰላም ፍለጋ መጥተው የጸኑበት፣ የኖሩበት አካባቢ መኾኑንም ገልጸዋል። እስልምና እና ክርስትና ተከባብረው ብቻ ሳይኾን ተስማምተው በፍቅር መኖር የቻሉበት መኾኑንም ተናግረዋል።
ተዝቆ የማያልቅ ታሪክ፣ ተዝቆ የማያልቅ ትምህርት የሚገኝበት ይህ አካባቢ ይሄን እሴት ከየት ተጎናጸፈው፣ ከየት ተማረው ብለን ታሪክ ስናገላብጥ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም የዚህ ሁሉ ምስጢር ኾኖ እናገኝዋለን ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት የነበሩ ኢትዮጵያውያን እና መሪዎች
የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን አስተምህሮ በውል ተገንዝበው ሰርተውበት ቢኾን ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ የት እንደምትኾን መገመት ትችላላችሁ ብለዋል።
የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሦስት ልዩ ዓላማዎች አሉት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደኛው ሥራ ነው፤ ሥራ የሚል ገዳም፤ ከሥራ ውጭ መለወጥ አይቻልም የሚል ገዳም ነው፤ ይሄን ደግሞ በመናገር ብቻ ሳይኾን ወደ ቅጥር ግቢያቸው ሲገባ በእርሻ ባሳዩት ውጤት ገዳሙ ሥራን የሚያስተምር ብቻ ሳይኾን ሥራ የሚሠራ ማኅበረሰብ ያለበት እንደኾነ ያሳያል ብለዋል።
ሁለተኛው የገዳሙ ዓላማ ትምህርት ነው፤ ዕውቀት ነው፤ የሐይቅ እስጢፋኖስ አባቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩ ግጭቶች፣ ወረራዎች፤ ወርቁን እንካችሁ መጻሕፍቶቻችን ግን አትንኩ ብለው ማጽናት መቻላቸውን ገልጸዋል።
ሦስተኛው የገዳሙ ዓላማ ጾም መኾኑን ተናግረዋል። ጾም ለስጋም ለመንፈስም እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፤ የሚጾም ሰው ስጋውን መግዛት ይችላል፤ ስጋውን በጥርሱ መንከስ ስለሚችል ከክፉ ነገር የተጠበቀ ይኾናል፤ የሚሠራ ሰው ለክፉ ነገር ጊዜ ስሌለው ከሚሠራው ፍሬ የተነሳ ውጤት እያየ ይሄዳል፤ ከክፉ ነገር ይጠበቃል፤ መጽሐፍትን የሚያገላብጥ፣ የሚያነብ፣ ለዕውቀት የተጋ፣ የተከፈተ አዕምሮ ያለው ሰው ከልማት እና ከትጋት ውጪ ለክፋት የተሰናዳ ስለማይኾን በሰላም እና በፍቅር ለመኖር ብቻ ሳይኾን የሀገርን ታሪክ ለማጽናት በእጅጉ የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ዓላማዎች በሐይቅ እስጢፋኖስ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ይህ ታሪክ በሁሉም ጫፍ የሚታወቅ እና ትምህርት የሚወሰድበት እንዲኾን ከታሪኩ ባሻገር ታሪክ ገላጭ ሥራዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት። ከታሪክ ገላጭ ሥራዎች መካከል አንዱ ይህ ሪዞርት ነው ብለዋል።
በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ከየትኛውም ጫፍ ጊዜውን ገንዘቡን ሰውቶ ሐይቅ የመጣ ሰው ታሪክ ሳይማር፣ ፍቅር ሳይጎነጭ፣ ደስታ እና ሰላምን ሳይከናነብ ወደ መጠባት አይመለስም ነው ያሉት።
በዚህ አካባቢ ስንቀሳቀስ ያስታዋልነው ታሪክ እና የሰው ፍቅር ብቻ ሳይኾን አየሩ በራሱ ሰላም ያለው፤ የማይጠገብ መኾኑን ነው ብለዋል። ወሎ የአራቱ ዜማዎች ቅኝት መገኛ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋዛ ፈዛዛ ቅኝት መገኛ መኾን እንደማይቻል ተናግረዋል።
የብዙ ታሪኮች፣ ባሕሎች፣ ቋንቋዎች፣ የብዙ ዘየዎች መገኛ ባይኾን የመቀበል እና የማስተናገድ ልምምድ ባይኖራችሁ ኖሮ አራቱ ዜማዎች ከዚህ አካባቢ ተፈጥረው ለዘመናት አይዘልቁም ነበር ነው ያሉት።
ወሎዬዎች በብዙ ነገር ይደነቃሉ፣ ይወዳዳሉ፤ ሰላም ይወዳሉ፤ ሰላም አንግቦ የመጣን ማቀፍ ይችላሉ፤ ይህ ፍቅራቸው እና ሰላም ወዳድነታቸው አካባቢያቸውን ማልማት እንዲችል ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
አሁን በሠራነው ሥራ ሳንረካ ከሠራን ሐይቅ ለብዙዎች የታሪክ ብቻ ሳትኾን የውበት መገኛም ትኾናለች ነው ያሉት። መንግሥት በታቸለው ሁሉ ከጎናቸው እንደሚኾንም ገልጸዋል። ለሐይቅ ከዚህ በላይ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። የሐይቅ ዙሪያን በአትክልት እና ፍራፍሬ ማልማት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በመልካም ለመወሳት እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም መልካም ሠርቶ መልካሙን አስተምሮ ማለፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ እንደ ወሎዬ ናት፤ ወሎዬ በፍቅር ሲመጡበት አርሂቡ ብሎ እጁን ዘርግቶ በፈገግታ መቀበል ይችላል፤ ወሎዬ በጸብ ሲመጡበት አጋ ለይ ይላል፤ ጸብን አንፈልግም፤ ጸብን አንሻም፤ ጸብ ከልማት፣ ከብልጽግና ያስተጓጉላል፤ ጉዟችንን ያራዝማል ነው ያሉት።
የምንፈልገው እንደ ወሎዬ በፍቅር የመጣውን አርሂቡ ብለን እጃችንን ዘርግተን ስቀን በፈገግታ መቀበል ማጉረስ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ነንና ደማችን ውስጥ አለና በጸብ ከመጡብን ደግሞ አጋ ለይ ማለታችን አይቀሬ ነው ብለዋል።
ጠላቶቻችን ስንሥቅ እና ሥንሠራ ለአርሂቡ ዝግጁ መኾናችንን እንድታውቁ፤ ስንጎነተል እና ስንነካካ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ነንና አጋ ለይ ማለት እንደምናውቅበት እንድትገነዘቡ መልዕክት አስተላልፋለሁ ነው ያሉት። ያማረ እና የበለጸገ አካባቢ በጋራ መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
