
ተፈጥሮ በልግስናዋ የውበት ካባ ላለበሰችው፣ ታሪክ በክብር ጌጥ ለኳለችው ደቡብ ወሎ፤ በ”ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት የተገነባው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ዛሬ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል።
ይህ ስፍራ የአብሮነት፣ የፍቅር እና የመቻቻል ተምሳሌት ለሆነው የወሎ ሕዝብ ተጨማሪ አዲስ የቱሪዝም ድምቀትና የልማት ዐቅም ነው። ሪዞርቱ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት በልማት የምንገልጥበት እና ለዓለም የምናሳይበት መስተዋት ጭምር ነው።
ሪዞርቱ ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የንግድና የአገልግሎት እንቅስቃሴውን በማነቃቃት፣ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገታችን ተደማሪ ጉልበት ይሆናል።
በተጨማሪም በአካባቢው ያሉ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መዳረሻዎችን ለሚጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች እንደ ዋነኛ መሸጋገሪያና መገናኛ ኮሪደር ሆኖ ያገለግላል።
ተፈጥሮ እና ታሪክ የለገሱንን ጸጋዎቻችንን ወደ ብልጽግና በመቀየር ረገድ የጀመርነው የሥራ ባህል ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ስኬት ብሎም ወደሚመጥናት ከፍታ ማሸጋገሩን ይቀጥላል።
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሐሳብ አመንጪነት በየአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ዐቅሞችን እየገለጥን፣ ከሕዝብ ጋር በስኬት ላይ ስኬት እየደረብን፣ ለላቀ ድል ከምናደርገው ትጋት ለአፍታ አንዝልም!
