“ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስትመንት እና የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትስስሮችን ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት” የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

8

 

አዲስ አበባ: ጥር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እና የንግድ ትስስር ለማጠናከር የብራዚል- ኢትዮጵያ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ከሁለቱም ሀገራት ባለሃብቶች፣ የንግድ መሪዎች እና ፖሊሲ አውጭዎች ተሳትፈዋል።

መድረኩ በሁለቱ ሀገራት መካከል የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማጉላት ዋና ዋና ዘርፎች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቴክኖሎጅ እና በቱሪዝም ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።

ጉባኤው ከባሕል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ባሻገር በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጠናከረ የኢኮኖሚ ግንኙነት መኖሩን የሚያንጸባርቅ መኾኑ ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ጃንዲር ፌሪዬራ ዶ ሳንቶስ ብራዚል በግብርና፣ በመሠረተ ልማት፣ በሰው ሀብት እና የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ እገዛ ታደርጋለች ብለዋል።

በጋራ መርህ ላይ ለተመሠረተ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብርን በማጠናከር ከ300 ሚሊዮን የተሻገረ የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ተጠቃሚ እናደርጋለን ነው ያሉት።

ፎረሙ በጋራ ግብ ላይ የተመሠረተ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ይረዳል ያሉት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር መለስ ዓለም ናቸው።

በኢትዮጵያ እና ብራዚል መካከል የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና ቴክኒካል ትብብርን ለማጠናከር እና ወደ ተጨባጭ ፕሮጀክቶች ለማሳደግ በሁለቱም ሀገራት በኩል እየተሠራ ነው ብለዋል።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ.ር) ስድስት አስርት ዓመታት የተሻገረውን ታሪካዊ የሀገራቱ ግንኙነት ለማጠናከር እና እንደ አህጉርም ለዘላቂ የጋራ እድገት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን በመጠቀም የብራዚል ኢንቨስተሮች እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ በንግድ ፣ በኢንቨስትመንት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ብራዚልን እንደ ስትራቴጂክ አጋር እንደሚቆጥር እውቅና ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ.ር) “ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስትመንት እና የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትስስሮችን ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት” ብለዋል። ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በማምረት፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በቴሌኮም፣ በባንኪንግ፣ በኃይል እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሠራች ስለመኾኗም ተናግረዋል።

ብራዚል በተለይ በአግሪ ቢዝነስ እና በምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፍ ላይ ያላትን ዓለም አቀፍ አቅም እና ልምድ በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት።

በጉባኤው የብራዚል ኦፊሴላዊ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ኤጀንሲ አፔክስ በብራዚል እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መካከል የመግባቢያ ሠነድ ተፈርሟል።

በተመሳሳይ የብራዚል የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ጋር የስምምነት ሰነድም ተፈራርመዋል።

ዘጋቢ:- መሠረት መቅጫ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቱርክዬ አምባሳደር እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በጋራ ለመሥራት ተወያዩ።
Next articleአዲስ አበባ በበጀት አጠቃቀም ከአፍሪካ ቀዳሚ ከተሞች ተርታ መሰለፏ ተገለጸ።