
ባሕር ዳር፡ ጥር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ አልምቶ ወደ ሥራ ያስገባቸውን የፕሮጀክት ማኔጅመንት አሥተደደር ሥርዓት (PMS) እና የቁልፍ ተግባራት የአፈጻጸም አመልካቾች (KPI) ሶፍትዌሮች የሥራ ማስጀመሪያ እያካሄደ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ያለንበት ጊዜ የዲጂታል ዘመን እና ለውጥ እንደ ጅረት የሚፈስበት በመኾኑ ተወዳዳሪ ቴክኖሎጅ መጠቀም ግድ እንደሚል ተናግረዋል። ዓለም በፍጥነት እየተለወጠ ነው፤ ዛሬ የሚመረቀው ቴክኖሎጅም በክልሉ አንድ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።
ከዚህ በፊት የክልሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታን ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ ለመምራት ብዙ ተግዳሮቶች እንደነበሩም አንስተዋል።
በክልሉ የ25 ዓመት የዘላቂ ልማት እና አሻጋሪ እቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ያስታወሱት ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ዕቅዱ መሬት የሚነካው በቴክኖሎጅ ሲደገፍ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት ሥራዎችን ሊያሳልጡ የሚችሉ ሶፍትዌሮችን ማልማት እና መጠቀም ደግሞ ግድ እንደሚልም ተናግረዋል።
ዛሬ የሚመረቁ ሶፍትዌሮች የክልሉ ሃብት እንዳይባክን፣ ፍትሐዊ በኾነ መንገድ እንዲመራ ለማድረግ እና የክልሉን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ትልቅ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት። በክልሉ የቴክኖሎጅ ልማት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል።
በቀጣይ አጠቃላይ ሥራዎች ዌብሳይት ላይ እንዲቀመጡ በክልሉ ኢኖቤሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እና ተጨማሪ የልማት መሠረት ኾነው እንዲያገለግሉ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ጥረት እንዲደረግም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፕሮጀክት አሥተዳደር ሥርዓቱ የክልሉ መንግሥት ወደ ሥራ የገቡትን ፕሮጀክቶች ያስተዋውቅበታል፤ አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ ይደረግበታል። የተቋማት የአፈጻጸም ምዘና ሶፍትዌር ደግሞ በክልሉ የሚከናወኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ለዕቅድ እና ለአፈጻጸም መለኪያ ኾኖ ያገለግላል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
