“ጥርን በባሕር ዳር” መርሐ ግብር የከተማዋን ገጽታ ለቱሪስቶች በመግለጥ ውጤታማ ነበር።

9
ባሕር ዳር፡ ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳርን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ”ጥርን በባሕር ዳር’ በሚል መሪ ሃሳብ በጥር ወር የተለያዩ ኹነቶች ሲከወኑ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ወጣት ፈንታ ጨቅሌ በባሕር ዳር የጀልባ ጉዞና ሽርሽር አገልግሎት ላይ ተሰማርቶ ቤተሰብ ያስተዳድራል።
ጥር እና የካቲት ወራት ምቹ የሥራ ወራት ቢኾኑም ”ጥርን በባሕር ዳር” በሚል ተሰይሞ ባሕር ዳርን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ጎብኝዎች የቆይታ ጊዜአቸውን በማራዘም ለሱም የኢኮኖሚ ምንጭ እንደኾነለት ገልጿል።
ጎብኝዎች ጥርን በባሕር ዳር እንዲያሳልፉ የተሠራው የማስተዋወቅ ሥራ የዘርፉን ተዋናይ መጥቀሙን አስረድቷል።
ባለፉት ዓመታት ሰው ለመንቀሳቀስ ስጋት እንደነበረበት እና በዚህ ዓመት የተፈጠረው ሰላም ግን ለእንቅስቃሴው ምቹ ኹኔታ መፍጠሩን ገልጿል። ይህም የተሻለ የሥራ ዕድል እንደፈጠረለት ነው የተናገረው።
የከተማውን እና አካባቢውን ሰላም በማስከበር ባሕር ዳርን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ይገባል ብሏል። ኅብረተሰቡም ለሰላም እና ጸጥታው ዘብ መቆም አለበት ነው ያለው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወነው የ”ጥርን በባሕር ዳር ” መርሐ ግብር በሂደት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም ከታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ ከባሕላዊ ክዋኔዎች እስከ ዘመናዊ ውድድሮች ድረስ የባሕር ዳርን ተፈጥሯዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ እሴቶች የሚያስተዋውቁ ሥራዎች ተፈጽመዋል። ይህም የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ጨምሯል ብለዋል።
ጎብኝዎችን ለማቆየት አካባቢውን ሰላም ማድረግ እና አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መሠራቱንም ነው አቶ ጋሻው የገለጹት።
የንግድ አውደ ርዕይ እና ባዛር፣ የባሕል እና ኪነጥበብ ፌስቲቫል፣ የገና ጨዋታ፣ አረጋውያንን እና ችግረኞችን የመደገፍ ሥራ፣ የመጽሐፍት ዐውደ ርዕይ፣ የብስክሌት እና የጀልባ ሽርሽር፣ የታንኳ ቀዘፋ ውድድር፣ የባሕል አውደ ርዕይ፣ የኪነ ጥበብ ምሽት እና የባሕል አለባበስ ትዕይንት፣ የጥምቀት እና ሌሎችም ሃይማኖታዊ በዓላትን ማክበር፣ በእሴቶች አጠባበቅ ላይ የፓናል ውይይት ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ይገኙበታል።
የአስጎብኝዎችን እና የአገልግሎት ሰጭዎችን አደረጃጀት ለማጠናከር ተሠርቷል፤ በዚህም የቱሪስቶች ቁጥርና ቆይታቸውን መጨመር ተችሏል ብለዋል።
በመኾኑም ጥርን በባሕር ዳር መርሐ ግብር ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ሰላሙ የበለጠ በመሻሻሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር ጨምሯል ያሉት አቶ ጋሻው ለቱሪስቶች ቤተሰባዊ አቀባበል በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥንም የማዘመን ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
የአስጎብኝ ድርጅቶች፣ የጀልባ፣ የታክሲ እና የሆቴል አገልግሎት ሰጭዎች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪ ለእንግዶች የሚመጥን መስተንግዶ ማድረጋቸውን መቀጠል እና መልካም ገጽታ ይዘው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአማራ ክልል የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ፎረም ምሥረታ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።