
ባሕር ዳር: ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የባሕርዳር እፅዋት ቲሹ ካልቸር ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
በአመልድ ኢትዮጵያ አማካኝነት የተቋቋሙው ባሕርዳር እፅዋት ቲሹ ካልቸር የሙዝና አናናስ ችግኝ፣ የድንች መሥራች ዘር፣ የቆላ ቀርከሃ፣ የተዳቀሉ አቮካዶ፣ ፓፓያና ቡና ችግኞችን በማባዛት በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮች እና አልሚ ባለሃብቶች እያቀረበ ይገኛል።
የእፅዋት ቲሹ ካልቸር ማዕከሉ በላብራቶሪ እና በችግኝ ጣቢያ በዓመት ከ3 እስከ 5 ሚሊዮን የደን፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን በማባዛት ለተጠቃሚዎች ያቀርባል።
በአራት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው ቲሹ ካልቸር ማዕከሉ ለትርፍ የተቋቋመ ብቻ ሳይኾን በዶሮ እርባታ፣ በወተት ላም፣ በዓሳ እርባታ እና ሌሎች የተቀናጁ ሞዴል ሥራዎችን በማከናወን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በሰርቶ ማሳያነት እያገለገለ ይገኛል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የእጽዋት ቲሹ ካልቸር ማባዣ ማዕከሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ለማስተዋወቅና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እያበረከተ ያለውን ጉልህ አስተዋፅዖ አድንቀዋል፡፡
ለዘመናዊ ግብርና እድገት አንደኛው የትኩረት መስክ የእፅዋት ቲሹ ካልቸር ልማት ዘርፍ እንደኾነ አንስተዋል።
የእፅዋት ቲሹ ካልቸር ልማት ለግብርና ምርታማነት፣ ለደን ልማት እና ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ አይተኬ ሚና ያለው ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡
ዘርፉ የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ መኾኑን ገልጸዋል።
ቲሹ ካልቸር ማዕከሉ አሁን ያለውን የውስጥ አቅምና የገበያ ፍላጎት መሠረት በማድረግ የምርት ጥራቱን ለማረጋገጥና ተደራሽነቱን ለማስፋት በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ከርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የባሕርዳር እፅዋት ቲሹ ካልቸር ማዕከል በሚፈለገው ደረጃ እንዲጠናከር የዘርፉ ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
