ለሀገር ክብር የተሠው የጀግኖች መኮንኖች አጽም በክብር አረፈ።

24
ሰቆጣ፡ ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሀገራቸው ሉዓላዊነት እና ክብር ሲሉ ሕይወታቸውን የገበሩ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መኮንኖችን አጽም የማሳረፍ ሥነ ሥርዓት በሰቆጣ ደብረ ገነት መድኃኒዓለም ደብር በክብር የማሳረፍ ተግባር ተከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ አቶ ወንድምአገኝ ማሞ ጀግኖቹ መተኪያ የሌላት ነፍሳቸውን ሰጥተው ላሳዩን ቁርጠኝነት እኛም ለሀገር አንድነት በመቆም አደራቸውን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ አለነ አድማሴ ሠራዊቱ ለአንዲት ኢትዮጵያ ነው የሚሞተው፤ ወጣቱ ትውልድም ከጀግኖች ሰማዕታት አንድነትን ሊማር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አምበሉ ጥላሁን ሠራዊቱ ለነፍሱ ሳይሳሳ ያስጠበቀውን ሰላም የአሁኑ ትውልድም በማጽናት ለተተኪው የማስተላለፍ ኀላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሩ ሜጄር ጄኔራል ሻንበል ፈረደ የዋግ ኽምራ ሕዝብ ለጀግኖቹ ለሰጠው ክብር እና ለአጽም ማሳረፍ መርሐ ግብሩ ላደረገው ትብብር ምሥጋና አቅርበዋል።
የጀግኖቹን አደራ ለማስቀጠል ዝግጁ መኾናቸውን የገለጹት ሜጄር ጄኔራል ሻንበል ፈረደ ሕዝቡም እንደተለመደው ከሠራዊቱ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት የጀግኖቹ አጽም በክብር አርፏል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleፋይዳ መታወቂያ የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ያሳድጋል።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የባሕርዳር እፅዋት ቲሹ ካልቸር ማዕከልን ጎበኙ።