
ባሕር ዳር፡ ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የክልሉ ሴቶች እና ፋይዳ መታወቂያ ማውጣት የሚችሉ ሕጻናት እንዲያወጡ ለማድረግ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ሒክማ ከይረዲን፣ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርዓያስላሴ እና የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ተገኝተዋል።
መድረኩን የከፈቱት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ሒክማ ከይረዲን መድረኩ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን አካታችነት በቁርጠኝነት የምናረጋግጥበት ነው ብለዋል።
ቀጣይ ሥራዎችም መታወቂያው የሚሰጥበት ብቻ ሳይኾን የሴቶችን አቅም መገንቢያም ጭምር እንደኾነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሴቶችን የመታወቅ መብት የምትተገብር ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ ሴቶች እና ሕጻናት ሌሎች የሚያገኙትን አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የባንክ እንቅስቃሴን፣ ብድር እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ለጤና እና ለትምህርት አገልግሎትም መታወቂያው የሚኖረውን ወሳኝነት ጠቅሰዋል።
የሴቶችን በሕግ የመታወቅ፣ ፍትሕ የማግኘት እና ከብዝበዛ ነጻ የመኾን መብትንም ያስከብራል ነው ያሉት።
ለዚህም የየደረጃው ሴት መሪዎች ሴቶች የመታወቂያው ተጠቃሚ እንዲኾኑ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮዳሄ አርዓያስላሴ ባስተላለፉት መልዕክት ፋይዳ መታወቂያ የመታወቅ መብትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ማንነትን የማረጋገጥ ተግባር እውን ያደርጋል። ለዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባትም አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
እንደ ሀገር ለ30 ሚሊዮን ሴቶች እና 10 ሚሊዮን ሕጻናት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት መታቀዱንም ገልጸዋል።
የመታወቂያው አለመኖር አገልግሎት ማግኘትን እና ተሳትፎን ሊገድብ እንደሚችልም ነው የገለጹት።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለሴቶች ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ሴቶች እና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመጠበቅም እንደሚረዳ ጠቅሰዋል።
መታወቂያው ከካርድ በላይ ነው ያሉት ኀላፊዋ ሴቶች ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነታቸውን የበለጠ እንደሚያረጋግጥም ገልጸዋል።
መታወቂያውን ለሴቶች ለማድረስም በዕቅድ እየተሠራ ነው። አገልግሎት ለማግኘትም ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ሁሉም አካላት እንዲረባረቡ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ሠብሣቢ ነጻነት ሲሳይ መታወቂያው በርካታ ጠቀሜታዎች ስላሉት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ትዕግሥት አበበ በከተማቸው ሥራው ከዚህ ቀደምም መጀመሩን አንስተዋል።
ከንቅናቄው መድረክ በኋላም እስከ ቀበሌ ድረስ በማውረድ ሴቶችን የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ እናደርጋለንም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
