የዜጎችን ሰብአዊ መብት በማስከበር እና የተፋጠነ ፍትሕ በመስጠት ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።

4
ባሕር ዳር: ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ዐቢይ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በማከናወን የተለያዩ ውሳኔዎች አሳልፏል።
የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት በሥራ የሚያገናኟቸው የጋራ ጉዳዮችን ተባብሮ እና ተቀናጅቶ ለመፈጸም እንዲያስችላቸው የጋራ የሥምምነት ማስተግበሪያ ቻርተር በመፈራረም ሥራውን የጀመረው በ2017 ዓ.ም ነበር።
በፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ቁጥር 297/2017 የሕግ ዕውቅና የተሰጠው የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ዐቢይ ኮሚቴ የ2018 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን በማከናወን የ6 ወራት የትብብር መድረኩ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ገምግሟል።
ኮሚቴው የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፉን የ6 ወራት አፈጻጸም በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። የክልሉን የፍትሕ መረጃ ማዕከል ማቋቋሚያ እና አሠራር መወሰኛ መመሪያ እና የማዕከሉን ማስተግበሪያ ድርጊት መርሐ ግብር ላይ ተወያይቶ ተጨማሪ ግብዓቶችን በመስጠት ለክልሉ የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ቦርድ እንዲቀርብም ውሳኔ አሳልፏል።
በግጭት እና ድኅረ ግጭት ወቅት የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎች ላይ በባለሙያዎች ሰነድ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ወስኗል፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ መግባባት ላይ ተደርሷል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲቲዩት የክልሉ የፍትሕ መረጃ ማዕከል ኾኖ በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለው የድርጊት መርሐ ግብርና የአፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ፣ በአባል ተቋማት መካከል ሊኖር ስለሚገባው የርእስ በእርስ ግንኙነት አግባብ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር የተደራጀው የትብብር መድረኩ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቢኒያም ዮሐንስ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማቱ የጋራ የኾኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ ዕቅድ በማቀድ በአሥራ አንድ ግቦች ሥር የተለያዩ ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን አመላክተዋል።
በዲጂታላይዜሽን፣ በሰብአዊ መብቶች አከባበር፣ የሪፎርም ሕጎች አተገባበር፣ በአቅም ግንባታና በወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ከሰብአዊ መብት አከባበር፣ ከተከሳሽና ምስክር አቀራረብ፣ ከአቅም ግንባታ ሥራዎች እና አንዳንድ የተቋም ኀላፊዎች በውይይቶች ተሳታፊ ያለመኾን ጉዳዮች ውስንነት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ውስንነቶቹ ላይ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተመላክቷል።
የአባል ተቋማቱ ኀላፊዎች ሰፊ ውይይት በማድረግ በውስንነት የተነሱ ጉዳዮችን መርምረው ሊስተካከሉ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በግጭት እና ድኅረ ግጭት የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የሚያጋጥሙ ተግድራቶች፣ መፍትሔዎች እና የተቋማቱ ሚና ላይ ተገቢው ጥናት ተደርጎ እና የማስፈጸሚያ ሰነድ ተዘጋጅቶ በትብብር መድረኩ አማካኝት ለክልሉ መንግሥት እንዲቀርብ ተስማምተዋል፡፡
የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲቲዩት የክልሉ የፍትሕ መረጃ ማዕከል ኾኖ እንዲያገለግል የተሰጠውን ኀላፊነት ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችለውን ረቂቅ የድርጊት መርሐ ግብርና የአማራ ክልል የፍትሕ መረጃ ማዕከል ማቋቋሚያና የአሠራር ሥርዓት መወሰኛ ረቂቅ መመሪያ በኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ሀሳቦች ተጨምረው ሰነዶቹ በኢንስቲቲዩቱ ቦርድ አማካኝነት የሚጸድቁ መኾናቸው ተመላክቷል፡፡
የመረጃ ማዕከሉ መቋቋም የዘርፉን ትክክለኛ አፈጻጸም ለማወቅ ፤ በመንግሥት ፣ በዘርፉ ተቋማት እና በሚመለከታቸው አካላት ለሚወሰዱ የዘርፉ ማሻሻያ እርምጃዎች እና የተለያዩ ውሳኔዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መኾኑ ተገልጿል።
የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ተቋማዊ ነጻነታቸው እንደተጠበቀ ኾኖ በጋራ እና በትብብር መሥራት የሚገባቸውን ሥራዎች ተባብረውና ተቀናጅተው በመሥራታቸው በዳኝነት እና ፍትሕ ስርዓቱ ላይ አዎንታዊ ለውጥ እየመጣ መኾኑን ገልጸዋል።
የዜጎችን ሰብአዊ መብት በማስከበር እና የተፋጠነ ፍትሕ በመስጠት ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ተቋማቱ አሁን ላይ መልካም የሚባል የሥራ ግንኙነት እንዳላቸው እና አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ጥቃቅን የአሠራር ክፍተቶችን በቶሎ እየፈቱ የኅብረተሰቡን የዳኝነትና የፍትሕ ጥያቄዎች ውጤታማ በኾነ መልኩ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የራያ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ጠብ የለበትም” የራያ ነዋሪዎች
Next articleበእንጅባራ ከተማ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው።