
ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ የሕወሃትን ትንኮሳ የሚቃወም ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
ሰልፈኞቹ ሕወሃት በራያ፣ በወፍላ እና ኮረም ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ወረራ አውገዘዋል። የሕውሃት ዳግም ወረራ እና ጦርነት ሊበቃ እንደሚገባም አንስተዋል።
የራያ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ጠብ የለበትም፤ ጠብ እየፈጠሩ ያሉት የሕወሃት ጥቅመኞች ናቸው፤ የፌዴራል መንግሥት ማንነታቸነን በሕጋዊ መንገድ ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል።
የሕወሃት የጥፋት ቡድን በኃይል እንዳፈናቀላቸውም ገልጸዋል። እኛ አማራ ነን ማንነታችን ይከበር እንጂ አማራ እንሁን አላልነም ነው ያሉት።
በሰላማዊ ሰልፉ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ታምራት ንጋቱ በጉልበት ማንነትን ለመጫን መሞከር የታሪክ ስህተት ብቻ ሳይኾን ትልቅ የእብሪት መገለጫ ነው ብለዋል።
የሕወሃት መሪዎች የሕዝብን ትዕግስት ወደጎን በመተው፣ የሰላም አማራጭን እንደ ድክመት በመቁጠር ለዳግም ወረራና ጦርነት በራያ ሕዝብ ላይ አቅደው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በራያ አካባቢ እየተደረገ ያለው ወታደራዊ ትንኮሳ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በግልጽ የጣሰ ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል።
ስዓቱ የልዩነት ሳይኾን የአንድነት ነው ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው ለሕልውናችን በጋራ በመቆም ለታሪካዊ ጥላቶቻችን የድል መግቢያ በር ሳንፈጥር በጋራ መታገል ይኖርብናል ብለዋል።
ከሰሜን ወሎ ዞን ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የትኛውንም የሃሳብ ልዩነት በጠረንጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በንግግር መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
