
ባሕር ዳር፡ ጥር26/2018ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ሥብሠባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ማኅበራዊ ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት በትምህርት ጉዳይ ላይ ባለፋት ዓመታት የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል ሥራ መሠራቱን እና የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ ሥራ ከተጀመረ ከስድስት እስከ ሰባት ዓመታት እንደኾነው ጠቁመዋል።
ቅድመ መደበኛ ላይ የመሠረተ ልማት የማሻሻል ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ቀጣይ ታች ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ጥራትን ለማሻሻል ሙከራ ተደርጓል፤ በቀጣይም ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ጥራት ለማሻሻል ትኩረት እንደሚደረግ በማብራሪያቸው ጠቁመዋል።
በሰላም ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች በተመለከተ አሁን ባለው ዓለም ውስጥ ልጆችን ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የከለከለ ታጋይ እና ነጻ አውጭ ምን ዓይነት መንግሥት እንደሚኾን ማሰብ በቂ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም አደገኛ ስብራት ነው፤ መግራት እና ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል።
የመምህራን ሥልጠና፣ ኑሮ እና ምዘናን ማሻሻል እንዲሁም ቴክኖሎጅን መጠቀም ትምህርትን የሚቀይር በመኾኑ ክህሎትን በቀጣይ ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የጤና ጉዳይን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት ከጥቂት ዓመት በፊት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ስምንት በመቶ መድኃኒት እናመርት ነበር አሁን ላይ 42 በመቶ እየተመረተ ነው ይህም ትልቅ እምርታ ነው ግን ብዙ ይቀራል ነው ያሉት።
የመድኃኒት ሥርጭት ችግር ስለመኖሩ ጠቅሰው ለችግሩ መፍቻ ሥርዓቶች እየተገነቡ እንደኾነም አስረድተዋል።
በጤና ተቋማት ሪፎርም ከፍተኛ እመርታ መጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤና ሴክተር ላይ የተሠራው ቆጠራ 10 ዓመት አልፎታል፤ አሁን የሚሠራው ግን ብዙ መረጃ አምጥቷል፤ ቀጣይ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ግን ይጠበቃል ብለዋል።
በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ከ37 በመቶ ተነስተው አሁን ላይ 61 በመቶ መድረሳቸውንም አስረድተዋል።
ከአንድ እና ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸውን ሕጻናት ሞት ስለመቀነሱም አስገንዝበዋል።
ማርበርግ በሽታ ላይ ቶሎ በማሳወቅ ሙያተኞችን በማሠማራት በተሠራ ሥራ ሦሥት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሽታውን መቆጣጠር ስለመቻሉም አስገንዝበዋል።
ጥቂት ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተምረው እና ሰልጥነው በመምጣት በሀገራቸው እያገለገሉ ነው፤ ለእኛው ጥቅም ሲባል ከእነሱ ጋር መቆም፣ እነሱን መደገፍ እና እንዲጠናከሩ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የጤና ጉዳዮች ላይ በጀት በመጨመር እና ግንባታን በማስፋት ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግም ነው ያስረዱት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
