
ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በተገኙበት መደበኛ ሥብሠባውን አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ( ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የአፍሪካ ቀንድ እንዳይቀደድ የተሰፋ፣ እንዳይጣመር የተቀደደ አካባቢ ነው ብለዋል። እንዳንለያይ እዚህም እዚያም አንድ ዓይነት ዘር፣ ቋንቋ እና ባሕል አለ፣ እንዳንጣመር ደግሞ ብዙዎቻችን ከብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የሌላ ጉዳይ አስፈጻሚ ነን ብለዋል።
ቀጣናው ብዙ ፍላጎት እንዳለበትም ተናግረዋል። የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ የተሳሳረ መኾኑን ገልጸዋል። ነገር ግን የሁለቱ ውኃዎች ጉዳይ አንዱ ላንዱ መከታ መኾን ሲገባው ጥይት አመላላሽ መኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የሚያስፈልጋት ለደኅንነቷ መኾኑን ነው ያነሱት። ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘላለሙ ተነጣጥለው መኖር አይችሉም ብለዋል።
ቀይ ባሕር ሃብቱ ትልቅ ስለኾነ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ መኾን እንደሚገባት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የጠየቀችው የፍትሐዊነት ጥያቄ መኾኑን ገልጸዋል። በሰላም እና በንግግር ቀይ ባሕርን ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ሰጥቶ በመቀበል እና በውይይት ቀይ ባሕርን መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል። በሰጥቶ መቀበል ተያይዞ ማደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ ላይ ፖርት ገንብቷል፤ ስንጣላ ሁሉም ቀረ፤ ስንታረቅ ኤርትራውያን በእኛ ፍርድ ቤት ቤታችን ስጡን አሉ፤ ሰጠናቸው፤ እኛስ በዚህ መንገድ አሰብን ብንወስድ ምን ችግር አለው ነው ያሉት።
እኛ ስጡን ብቻ አላልንም፤ የቀረ ነገር ካለ ውሰዱ ብለናል፤ ነገር ግን በቀጣይነት ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ጸጋዋ ማስቀረት አይቻልም፤ ኢትዮጵያን ከመንገዷ ማንም አስቁሟት አያውቅም፤ ማንም ሊያስቆማትም አይችልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያን መጉዳት የሚሹ ሀገራት ማወቅ ያለባቸው ኢትዮጵያን ጎድቶ አሸናፊ እና ትርፋማ መኾን እንደማይቻል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ስንነካ በምድራችን ብቻ ሳይኾን የእኛ ምድር በሚባለው ሁሉ ችግር ፈጣሪ መኾናችን አይቀሬ ነው፤ ይህ እንዳይኾን ተግባብቶ መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል። ለእኛ የሚገባንን በቀጣይነት መከልከል እንደማይቻል ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ ጥያቄ ተገቢ መኾኑን ማመኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለመወያየት እና በንግግር ጥያቄዋን ለማስፈታት ዝግጁ መኾኗን ገልጸዋል።
በዲፕሎማሲ፣ በብሔራዊ ጥቅም ማስከበር መልካም ጅማሮዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። የባሕር በር ተጠቃሚነት ግን በባሌም ይሁን በቦሌ አይቀርም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
