
ባሕር ዳር: ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብረታቦር ከተማ እየተከበረ ነው።
በበዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ዛሬ የታሪክ፣ የባሕል፣ የሃይማኖት፣ የጸና ኢትዮጵያዊነት እና የጀግንነት ሕያው ምስክር በኾነችው ደብረታቦር ተገኝተናል ነው ያሉት።
ማማው ደብረ ታቦር እና አካባቢው ባሕል እና ማንነት ድር እና ማግ የኾኑበት፤ ታሪክ እና ጀግንነት የተንሰላሰሉበት፤ እንደ መልካ ምድራዊ ገፅታው ታማኝነቱ እና ሀገር ወዳድነቱ ከፍ ብሎ የተቀመጠበት ነው ብለዋል።
በዚህ አካባቢ ሀገር ወዳድነት እና ለሀገር መታመን ሞልቶ እንደሚፈስ ታሪክ ዛሬም ጥንትም በቂ ምስክር ኾኖ እንደሚናገርም ገልጸዋል።
በአጼ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግሥት እንደተመሠረተች የሚነገርላት ጥንታዊቷ “ጁራ” የአሁኗ ደብረ ታቦር በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ እጥፋት ውስጥ የዘመነ መሳፍንት ማክተም ብስራት ተደርጋ እንደምትወሰድ አንስተዋል።
በጋፋት አጼ ቴዎድሮስ፣ በአሪንጎ አጼ ሱስንዮስ፣ በሰመርንሃ አጼ ዮሐንስ ከከተማዋ እና ከአካባቢው ታሪክ ጋር ስማቸው እና አሻራዎቻቸው ሕያው ምስክር ኾነው ዛሬም ድረስ እንደሚታዩ ገልጸዋል።
ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የመንግሥታቸውን መቀመጫ በደብረ ታቦር ሲያደርጉ በርካታ ሕዝብ በዙሪያው መስፈሩን እና መክተሙን ተከትሎ ለመስፋቷ ዕድል እንደፈጠረም ይታመናል ነው ያሉት።
ደብረ ታቦር እና አካባቢው ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ምሥረታ ዕውን መኾን ፈር ቀዳጅ አካባቢ ነው ብለዋል። የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አንጥረኛ እና መሐንዲስ በነበሩት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ አማካኝነት ኢንዱስትሪ በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረባት የጋፋት መገኛ፣ የሥልጡን ማኅበረሰብ መክተሚያ፤ የሥልጣኔም መጀመሪያ እንደኾነች አንስተዋል።
የተክሌ አቋቋም መገኛ የኾነው ይህ አካባቢ የጥበብ መዲናም ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት። ደብረ ታቦር እና አካባቢው በሀገረ መንግሥት ምሥረታ እንደ ራስ ጉግሳ ወሌ፣ በታማኝነት እና በጀግንነት እንደ ፊታውራሪ ገብርየ፣ በሊቃውንት እንደ አለቃ ገብርሃና እና ደስታ ተገኝ ሀገራዊ አበርክቶ ያላቸው የሀገር ባለውለታዎች መገኛ ነውም ብለዋል።
ሹመት ሲሰጠው ሹመቱ ለእኔ ቀርቶ ለአካባቢየ ይሰጥልኝ ያለ ሀገር ወዳድ እና ሀገሩን በክብር የሚያስጠራ የጦር ፊታውራሪ መገኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዛሬ የመጣነው የሰማዕቱን ቅዱስ መርቆሪዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓልን በታሪካዊው የአጅባር ሜዳ እንዲህ በደመቀ መልኩ ለማክበር ነው ብለዋል።
የተፈጥሮ ሕግ ኾኖ በአንድ ጊዜ ሁለት ቦታ ላይ መገኘት አልታቸለም እንጅ የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሪዎስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በመካነ ኢየሱስ ከተማም በድምቀት እየተከበረ መኾኑን ገልጸዋል። በዚያም መገኘት ብንችል ኖሮ ደስታችን ወደር አልነበረውም ነው ያሉት። መልካም በዓል የሚለው የመልካም ምኞት መልዕክታችን ግን ባላችሁበት ይድረሳችሁ ብለዋል።
ጥንታዊው እና ታሪካዊው የአጅባር ሜዳ የደብረ ታቦር ከተማ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ የታሪክ፣ የባሕል፣ የጀግንነት እና ሃይማኖታዊ ሁነቶች አደባባይ መኾኑንም ገልጸዋል።
አጅባር ሜዳ ልበ ሰፊ ነው፤ ከጥንት እስከ ትናንት ብዙ ነገሮችን አይቷል፤ እልፍ ትዕይንቶችን አስተናግዷል ነው ያሉት። አጅባር ከሚያስተናግዳቸው ሁነቶች መካከል ደግሞ በየዓመቱ ጥር 25 ቀን የሚከበረው የቅዱስ መርቆሪዎስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል አንዱ መኾኑን ተናግረዋል።
የቅዱስ መርቆሪዎስ ዓመታዊ በዓል ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ነው ያሉት ኀላፊው አከባበሩ ግን በባሕላዊ የፈረስ ጉግስ እና የፈረስ ግልቢያ ውድድር ጨዋታዎች የታጀበ ነው ብለዋል። በበዓሉ አከባበር ላይ የሚካሄደው የፈረስ ግልቢያ እና የጉግስ ጨዋታ ልብ አንጠልጣይ ትንቅንቅ የሚታይበት ማራኪ ትዕይንት መኾኑን ገልጸዋል።
በፈረስ ትርዒቱ ላይ ካስደሳች ትዕይንት የዘለለ መመታት ቢኖር እንኳ ቂም እንደማይያዝ ነው የተናገሩት። ምናልባትም ይህ የጉግስ ጨዋታ የማኅበረሰቡን የቆየ የሥነ ልቦና ከፍታ እና የመንፈስ እርጋታ የሚወክል ትዕይንት ሳይኾን አይቀርም ነው ያሉት።
ጨዋታው ሲጠናቀቅ አሸናፊም ኾነ ተሸናፊ፤ ቀዳሚም ኾነ ተቀዳሚ በዓሉን በጋራ እያደመቁ በአብሮነት መዝለቃቸው ሰፋ ተደርጎ ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ ቢጠና የሚነግረን ሌላ የአሸናፊነት መሠረት ይኖረዋል ብለዋል።
በክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት እንደኾነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይነግሩናል ያሉት ኀላፊው ዛሬ በአጅባር አደባባይ እንዲህ ተሠባሥበን በጋራ እና በድምቀት የምናከብረው በዓል የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሪዎስ የንግስ በዓል ነው ብለዋል። ላመኑበት፣ ለሚኖሩበት እና ለሚቀበሉት ዕውነት ዋጋ የከፈሉልን ሁሉ ማክበር ባሕላዊ ብቻ ሳይኾን ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው መኾኑንም እንረዳለን ነው ያሉት።
ይህ በዓል ከሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሪዎስ ንግስ ጋር ተያይዞ የሚከበርበት ምክንያትም፤ ቅዱስ መርቆሪዎስ ለሃይማኖቱ በፈረስ ላይ ኾኖ ያደረጋቸውን ተጋድሎዎች እና የተቀዳጀውን ድል ለማዘከር ነው ብለዋል።
ቅዱስ መርቆሪዎስ ለሚያምንበት ሃይማኖት እና ዕውነትም እስከ መጨረሻው በጽናት ይቆማል፡፡ በአሳዳጆቹ እጅ ያልፋል፤ ነገር ግን እንዲህ ዘላለማዊ ኾኖ ይዘከራል፡፡ ዛሬ በዚህ አደባባይ የሰማዕቱን ዓመታዊ የንግስ በዓል ለመታደም የቆምን ሁሉ የምንማረው እና የምንመረምረው ዕውነት ቢኖር ላመኑበት በጽናት፣ ለሚከተሉት በብርታት፣ ለሚከውኑት በትጋት መፈጸምን ነው ብለዋል።
በአጅባር ሜዳ በፈረስ ትርዒት የታጀበው ዓመታዊ የቅዱስ መርቆሪዎስ የንግስ በዓል አከባበር ረጂም ዕድሜ እንዳለው አንስተዋል።
በዓሉን ከሃይማኖታዊ መሠረቱ እና ከባሕላዊ እሴቱ ሳይርቅ ጠብቆ መዝለቅ አንድ ስኬት መኾኑን ገልጸዋል። በዓሉን በሰፊው ማስተዋወቅ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ እና ማልማት ላይ ግን እያንዳንዳችን ለነገ የምንሠራው ሥራ ነው ብለዋል።
የሀገር ብልጽግና መንገድ ከኾኑት አምዶች መካከል አንዱ ቱሪዝም መኾኑንም ተናግረዋል። መንግሥት የሕዝብን እሴት በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና በማሳደግ ለትውልድ ግንባታ እና ለዘላቂ ልማት ማዋል እንደሚገባ እንደሚያምንም ተናግረዋል።
የቱሪዝም ጸጋዎችን እያለማ መኾኑንም ገልጸዋል። የአካባቢው ተወላጆች እና መላው ኢትዮጵያውያን አካባቢው ላይ ያለውን የመልማት ዕድል በመጠቀም እንዲያለሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
