
ባሕር ዳር: ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የኾኑ አስፈጻሚ አካላትን የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ዛሬ ገምግመናል ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የብልጽግና ዕሳቤ መሬት ነክቶ ፍሬ እያፈራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተቋማትና የተቋማት መሪዎች ግንባር ቀደም ተዋንያን ናቸው ነው ያሉት።
የብልጽግና ጉዞ “እየሠራሁ ነው፤ ልሠራ ነበር፤ በመሥራት ላይ ነኝ”፤ የሚሉ ሪፖርቶችን አይቀበልም፡፡ ከተሠራ መታየት፤ ከተከናወነ መዳሰስ አለበት ብለዋል።
በ2018 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አጠናቀን በጉባ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አብስረናል። የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን፣ የነዳጅ እና የማዳበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምረናል ነው ያሉት።
መንግሥታችን ጀምሮ በፍጥነት መጨረስ መለያው ነው፤ በዚህ እሳቤ የተጠናቀቁትን ሸበሌ ሪዞርትንና አይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫን አስመርቀናል፡፡ በቅርቡም የምናስመርቃቸው አሉ፡፡ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ግድቦች፣ ቤቶች፣ እየተገነቡ ናቸው፡፡ የጉባ ብሥራቶች ቀስ በቀስ ሥር ሰድደው ተግባራዊ እየኾኑ ናቸው ብለዋል።
በዛሬው ግምገማችን የሥራ እንቅስቃሴዎቻችንን እና ስኬቶቻችንን በልኩ መዝነናል፤ ድክመቶቻችንን ያለ ምሕረት ለማረም ተግባብተናል፤ የመፍትሔ መንገዶችን የሚያመላክት እና አዳዲስ ስልቶችን ለመንደፍ የሚያስችል ገንቢ ምክክር አድርገናል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት እና በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ባስመዘገብነዉ ድል ሳንኩራራ ነገር ግን በልኩ እየተበረታታን በቀጣይ ስድስት ወራት ለላቀ ውጤትና ድል ለመትጋት ተግባብተናል ብለዋል በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
