“እምቢ ለዳግም ባርነት” የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ

78
ሁመራ፡ ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በአራቱ ወረዳዎች እና በአምስቱ ከተማ አሥተዳደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች የህወሃትን የዳግም ወረራ ፍላጎት እና የጦርነት እንቅስቃሴ የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰላማዊ ሰልፉ “እምቢ ለዳግም ባርነት” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሄደው። በሰልፉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ሰልፉ ሦስት ዓላማዎች እንዳሉት ገልጸዋል።
እነዚህም “ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ መኾኑን፤ የህወሃትን ጦር ሰባቂነት እና ተስፋፊነት የማውገዝ እንዲሁም ሕዝቡ እና የዞኑ አሥተዳደር ከፌዴራል መንግሥቱ ጎን መቆሙን የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀገራችንን ለመምራት የሚመጥኑ እና ውስጣዊ ችግሮቻችንን ተረድተው በመፍታት ወደ ከፍታ እንደሚያደርሱን በማመን የዞኑ ሕዝብ እና አሥተዳደር ከጎናቸው ይቆማል ነው ያሉት።
እኛ ሰላም እንጅ ጦርነት አንፈልግም ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የህወሃትን ጸረ ሰላም እንቅስቃሴ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊቃወመው እንደሚገባም አመላክተዋል።
በሰላም እንጅ በጉልበት የሚሳካ ነገር ባለመኖሩ ህወሃት እና ጦርነት በቃን ሊባል ይገባል” ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ወሰን እና ማንነቱን ለማስከበር እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ቆርጦ ተነስቷል ያሉት ደግሞ የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ ናቸው።
ከነጻነት በፊት ህወሃት በወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ላይ ያልፈጸመው ግፍ እና በደል የለም ብለዋል። አሁንም ያንን ግፍ እና በደል ለመድገም በማለም፤ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ላይ የዳግም ወረራ እንቅስቃሴ እያደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
ሕዝቡም ነጻነቱን አሳልፎ ላለመስጠት እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመኾን ሀገርን እንደሚያስከብር ገልጸዋል። አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም ያሉት ደግሞ የሰልፉ ተሳታፊዎች ናቸው። ህወሃት ተከዜን ተሻግሮ ለዳግም ወረራ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በሰላማዊ ሰልፍ ለማውገዝ መውጣታቸውን የገለጹት ተሳታፊዎቹ ነጻነታቸውን ለመጠበቅ እና ማንነታቸውን ለማስከበር ዝግጁ መኾናቸውን አንስተዋል።
“እምቢ ለዳግም ባርነት”፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኩራታችን ነው፤ የጦርነት አዙሪት እና ህወሃት በቃን፤ ሁላችንም የተከዜ ዘቦች ነን፤ የሀገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝን የሚሸከም ትክሻ የለንም፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል፤ ለዘላቂ ሰላም እና አብሮነት በጽናት እንቆማለን፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተሟላ ሁኔታ ይተግበር እና ሌሎችም መልዕክቶች በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ ተስተጋብተዋል።
ዘጋቢ፦ ምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ደብረ ታቦር በአፍሪካ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ መንደር የተገነባባት የአጼ ቴዎድሮስ የህልሙ ተጋሪ ከተማ ናት” አቶ መልካሙ ጸጋየ
Next article“የብልጽግና ጉዞ እየሠራሁ ነው፤ ልሠራ ነበር፤ በመሥራት ላይ ነኝ፤ የሚሉ ሪፖርቶችን አይቀበልም” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ