
ባሕር ዳር: ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፈረሶች እና ፈረሰኞች ትርዒት የሚደምቀው የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓል በታሪካዊቷ ደብረ ታቦር ከተማ እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋየ ደብረ ታቦር የበጌምድር ፈርጥ፣ የአጼ ቴዎድሮስ መናገሻ፣ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ መንደር ሠሪ፣ የሊቃውንት መገኛ፣ የባሕላዊ እና የተፈጥሮ ጸጋዎች ማዕከል መኾኗን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የድል ተምሳሌት እና በኅብረብሔራዊነት የደመቀች ታላቅ ሀገር ናት፤ ያላትን እምቅ አቅም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለማኅበረሰብ ዕድገት በመጠቀም ረገድም ባሕል ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል። ባሕል ሰላምን በማስፈን በሕዝቦች መካከል አብሮነትን እና ትስስርን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
አማራ ክልል በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች የሚታደሙባቸው ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት ያሉበት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
እነዚህ ዓመት ጠብቀው የሚመጡ በዓላት የአማራን ሕዝብ ባሕል እና እሴቶች በመጠበቅ ትውልዱ በጠንካራ ማንነት ላይ እንዲቆም የሚያበረክቱት ሚና ከፍተኛ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
በዓላቱ ባላቸው ተወዳጅ ክዋኔ ምክንያትም ሚሊዮኖች በጉጉት ጠብቀው የሚታደሙባቸው ሃብቶች ኾነዋል። ለሚከበሩባቸው አካባቢዎችም ከማኅበራዊ መስተጋብር በተጨማሪ የኢኮኖሚም ምንጭ ናቸው ብለዋል ቢሮ ኀላፊው።
ደብረ ታቦር ከተማ ታሪክ የማይሽራቸው፣ ትውልድ የሚኮራባቸው እና ቀልብን የሚስቡ ታሪካዊ እና ሃይማኖት ቅርሶች ባለቤት ናት ብለዋል። ደብረ ታቦር ከላይ ጉና፤ ከታች ጣና የከበቧት የጸና ኢትዮጵያዊነት ማኅደር ናት” ሲሉም ተናግረዋል።
ከተማዋ በአፍሪካ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ መንደር የተገነባባት መኾኗ ለአጼ ቴዎድሮስ ከመናገሻነትም አልፋ የህልሙ ተጋሪ ከተማ ስለመኾኗም ምስክር ነው ብለዋል።
ዛሬ የሚከበረው የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓልም ከተማዋ የሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሁነቶች ማዕከልነቷን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። የበዓሉ ማክበሪያ አጅባር ሜዳም በኪነ ጥበብ ሥራዎች ከፍ ብሎ የሚታወቅ ታሪካዊ ቦታ ነው፤ ልዑል ዓለማየሁ የተወለደው በዚሁ ነው፣ የደጃዝማች አያሌው ጦር ከሰሜን መልስ እዚሁ ነው ያረፈው ብለዋል።
ደብረ ታቦር ከተማም ይህንን ታሪካዊ ቦታ ጠብቃ እና የታሪክ መዘክር እንዲኾን ከልላ ይዛዋለች ነው ያሉት። በፈረስ ጉግሥ እና ሽርጥ፣ በተክሌ አቋቋም ዝማሜ፣ በወጣቶች ዝማሬ እና ሆታ የሚደምቀው የመርቆሬዎስ በዓል በደብረ ታቦር አጅባር ሜዳ እና በእስቴ መካነ ኢየሱስ ዴንሳ ተራራ ስር ዛሬ እየተከበረ ነውም ብለዋል። በዓሉ ለደቡብ ጎንደር ብቻ ሳይኾን ለክልሉ እና ለሀገር ቱሪዝምም ትልቅ ጸጋ በመኾኑ መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዓላትን ጠብቆ፣ አልምቶ እና እሴታቸውን አጉልቶ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሁሉንም ዜጋ ድርሻ ይጠይቃል ብለዋል። የሁነቶችን ክዋኔ ሰንዶ ለመያዝ፣ ጥናት እና ምርምሮችን ለመሥራትም የተቋማት ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
የበዓላቱ ዋነኛ ባለቤት የኾነው ማኅበረሰብ ደግሞ በንቃት እና በስፋት ተሳታፊ በመኾን የበኩሉን መወጣት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
