
ባሕር ዳር: ጥር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የአርሰናል እና የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋች ባካሪ ሳኛ የባሕር ዳር ስታዲየምን ጎብኝቷል። በጉብኝቱ ከባካሪ ሳኛ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።
የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች ባካሪ ሳኛ በኢትዮጵያ ቆይታው አስደናቂ ቦታዎችን መጎብኘቱን ተናግሯል። በባሕር ዳርም የሚያምረውን የባሕር ዳር ስታዲየም ማየቱን ነው የገለጸው። ስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ ነው፤ ለዚህ ደግሞ እኔ ምስክር ነኝ ነው ያለው።
የባሕር ዳር ስታዲየምን የመልበሻ ክፍል፣ የሜዳውን ሳር እና ሌሎችን ተዘዋውሮ መመልከቱን ገልጿለወ። ስታዲየሙ በርካታ ጨዋታዎችን ማጫወት የሚችል ደረጃውን የጠበቀ መኾኑን ተናግሯል።
ስታዲየሙ ምን አልባትም በምሥራቅ አፍሪካ ምርጡ ቦታ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት ያለው ባካሪ ሳኛ የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት እንደምትችልም አንስቷል። ኢትዮጵያ የተለያዩ ታሪኮች እና ባሕሎች ያሏት ሀገር ናት፤ ይሄን ደግሞ ማሳየት አለባት ነው ያለው።
ኢትዮጵያ የታሪክ እና የባሕል ሃብታም መሆኗንና እግር ኳስን የሚወድ ሕዝብ ያላት ሀገር እንደሆነች ተናግሯል። ለተሻለ እግር ኳስ የተሻለ የስፖርት መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልግም አመላክቷል።
ተጫዋቾች የሚነሱበት ሃብት ለእግር ኳስ አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም፤ እኔ ለዚህ ምሳሌ ነኝ፤ እስከ 15 ዓመቴ ድረስ በሳምንት አንድ ቀን ነበር ልምምድ የምሠራው፣ ነገር ግን በታላቅ ደረጃ ከመጫወት አላገደኝም ነው ያለው።
እንደ ሀገር ግን ታዳጊዎችን በሥልጠና እና በሌሎች ጉዳዮች መደገፍ እንደሚያስፈልግም ገልጿል። ሥልጠና እና መሠረተ ልማት ለእግር ኳስ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ተናግሯል።
ባካሪ ሳኛ በባሕር ዳር ስታዲየም ከታዳጊዎች ጋርም እግር ኳስ ተጫውቷል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
