
ባሕር ዳር: ጥር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ክልሉ “አርቆ ማየት አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት የ25 ዓመት አሻጋሪ እቅድ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ይዞ ለሁለንተናዊ ብልጽግና እየሠራ ነው ብለዋል። ያለፉ ስድስት ወራትም ዕቅዱ ተግባራዊ መደረግ የተጀመረባቸው እንደነበሩ ጠቁመዋል።
በችግሮች ታጥሮ መቆም አያስፈልግም፤ ከተለመደው እይታ መውጣት እና ከችግሮች በላይ ኾኖ ለልማት መሥራት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
“ሕዝባችንን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ የሚያስችል ምናብ ይዘን እና አሳሪ ችግሮችን በጥበብ እየተሻገርን ሥንሠራ ቆይተናል፤ እንቀጥላለንም” ብለዋል።
አርቆ ማየት፣ አልቆ መሥራት ብለን የተነሳነውም ችግሮችን በልዩ እይታ ፈትሾ ለማስተካከል፣ መልካም ዕድሎችን ደግሞ እንደመስፈንጠሪያ ተጠቅሞ ታላሚውን እድገት ለማስመዝገብ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በተለመደው አካሄድ ሠርተን ሕዝባችንን ማሻገር ያዳግታል፤ ተደማሪ ሥራዎችን ማከናወን ግድ ይላል፤ ተደራራቢ ችግሮችን ተሻግሮ ከፍታ ላይ ለመቆም አልቆ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዋነኛ ሥራችን ሃብትን ፈጥረን የሕዝብን ኑሮ ማሻሻል ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “በውስን ሥራ እና ውጤት ታጥረን አንቀመጥም በግብርና፣ በማዕድን እና በሌሎችም አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ በስፋት ወደ ማምረት መግባት አለብን ነው ያሉት።
ይህ በስፋት የማምረት ሥራ ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ዘርፎች ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል። በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሠርተው ውጤት የተገኘባቸው ሥራዎች እንደ ሀገር ተመስግነዋል፤ እንደ ክልልም በልህቀት ሥንሠራ ተጨባጭ ለውጥ እንደምናጣ ትምህርት ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት።
የተከናወኑ ሥራዎችን የበለጠ ለማሳደግ ደግሞ በጥልቀት መገምገም፣ ችግሮችን መቅረፍ እና ዕድሎችን ደግሞ እንደመስፈንጠሪያ ተጠቅሞ በትጋት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነት ቅነሳ፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እና አቅመ ደካሞችን መደገፍ ላይ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም አሁንም ገና ብዙ መሥራት የሚገቡ ሥራዎች አሉና በደንብ መገምገም እና በትኩረት መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
