ኢትዮ ቴሌኮም በስድስት ወሩ 85 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

5
አዲስ አበባ: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ገምግሟል።
ባለፉት ስድስት ወራት ተቋሙ 85 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል። 35 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግብር መክፈሉንም ተናገረዋል።
የደንበኞችን ቁጥር፣ እርካታ ማሳደግ እና የአገልግሎት ጥራት እና የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት ላይ በትኩረት መሠራቱንም ሥራ አሥፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 278 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያ በመገንባት የነበሩ ጣቢያዎችን ቁጥር ወደ 10 ሺህ 288 ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት።
በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል 102 ወረዳዎችን፣ 332 ቀበሌዎችን የሚያገናኙ 130 የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተዋል ብለዋል።
በመሠረተ ልማት ዝርጋታ 253 ኪሎ ሜትር የሜትሮ አገልግሎት ዝርጋታ ተከናውኗል ነው ያሉት። አማራጭ የኃይል ምንጭ በመጠቀም የገጠሩን ክፍል ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል።
32 ሺህ 960 ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ እንዳይገጥማቸው ከኮፐር ወር ፋይበር መቀየር ተችሏል ነው ያሉት። የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን የማስፋት ሥራም በትኩረት ተሠርቷል ብለዋል።
47 ሺህ ስልኮችን ለደንበኞች በተመጣጣኝ ዋጋ እና የተለያያ የክፍያ አማራጭ በማቅረብ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 45 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።
ኢትዮ ቴሌኮም ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ በኾነው ቴሌ ብር 58 ነጥብ 61 ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቷል፤ 6 ነጥብ 88 ትሪሊዮን ብር በቴሌ ብር ተንቀሳቅሷል ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር 87 ነጥብ 1 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ሰላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የአፈጻጸም ጉድለት ያለባቸውን ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት ይሠራል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next article“ከችግር ለመውጣት ሁሉም አካላት ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን አቀናጅተው መሥራት አለባቸው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)