
ባሕር ዳር: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመሠረተ ልማት ዘርፍ ተቋማት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ተገምግሟል፡፡
በግምገማው በመንገድ፣ በመጠጥ ውኃ፣ በመስኖ፣ በኤሌክትሪክ እና በቴሌኮም አገልግሎት እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው ተመላክቷል።
በተለያየ ምክንያት የአፈጻጸም እና የተደራሽነት ችግር ያለባቸውን የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በመለየት መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ ቀለምወርቅ ምሕረቴ ተቋማቱ ያላቸውን አቅም በውል በመለየት ለተሻለ ውጤት መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ለአንዳንድ ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት የኾኑ የወሰን ማስከበር እና በካሳ ክፍያ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን በፍጥነት መፍታት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ ነው ያሉት አማካሪው በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ያለባቸውን ግብዓት ለማሟላት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ የመሠረተ ልማት አማካሪ ደሴ አሰሜ የመሠረተ ልማት ዘርፍ ተቋማት ዕቅድ አፈጻጸም ለውጥ የታየበት ነው ብለዋል።
ግንባታቸው የተጠናቀቁ እና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የመንገድ፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ለክልሉ ዕድገት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ እንደኾኑም አንስተዋል።
በፌዴራል እና በክልል ፕሮጀክቶች መካከል ያለው አፈጻጸም ልዩነት ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ደሴ በኮንትራት አሥተዳደር በኩል የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ሁሉንም ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የሕዝብን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ መመለስ በሚችል ዕቅድ ላይ ተመስርቶ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ እና ጥራት ማጠናቀቅ የምርጫ ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት።
በተያዘላቸው ጊዜ መፈጸም አለመቻል የመልካም አሥተዳደር ችግር ብቻ ሳይኾን የፍትሐዊነት ጉዳይ መኾኑን መረዳት ይገባል ብለዋል።
የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ለማድረግ የዘርፉ ተቋማት ዝግጁ በመኾን ሁሉንም አካቶ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በጸጥታ ምክንያት የአፈጻጸም ጉድለት ያለባቸውን ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት የክልሉ መንግሥት የድርሻውን እንደሚወጣ አመላክተዋል።
ከርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በቀጣይ የተገኙ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና የታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት ለማረም የተቀናጀ የክትትል እና ድጋፍ ሥራን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
