
ባሕር ዳር: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአሁኑ ወቅት ዓለምን ድንበር ሳይለይ እየፈተነ የሚገኘው የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ የሀገራት የልዕለ ኀያልነት መገለጫም እየኾነ መጥቷል።
ግሩፕ አይ.ቢ በመባል የሚታወቀው እና ትኩረቱን የሳይበር ጥቃቶችን በመመርመር፣ በመከላከል እና የዲጂታል ወንጀሎችን በመዋጋት ላይ ያደረገው ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ተቋም በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ለሰው ልጅ በርካታ ጠቀሜታዎችን እየሰጠ ቢኾንም ለሳይበር ጥቃት ግን አዲስ እና አደገኛ ማዕበል እየቀሰቀሰ መኾኑን ያትታል፡፡ እያቀጣጠለው ያለው አደጋም አምስተኛው የሳይበር ጥቃት ማዕበል የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
እንደ ተቋሙ ሪፖርት ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ የሳይበር ጥቃት የተለያዩ የለውጥ ምዕራፎችን አልፏል። ይህም ከፊሽንግ ጥቃት ጀምሮ እስከ ውስብስብ የጥቃት ምዕራፎችን ያካትታል።
አምስተኛው የሳይበር ጥቃት ማዕበል የሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንደ መሳሪያ በመጠቀም የሚፈጸም ነው። አምስተኛ የተባለበት ምክንያት ደግሞ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለዚህ አገልግሎት መጠቀም ከተጀመረበት ጊዜ በፊት 4 የለውጥ ምዕራፎች ስላለፉ ነው፡፡
በ1990ዎቹ የነበሩ ሃከሮች በኮምፒውተር ቅንብር የሚያዘጋጇቸው የፊሽንግ እና የቫይረስ ጥቃቶች የመጀመሪያዎቹ ነበሩ። በ2000 ዓ.ም መጀመሪያ የነበሩ ለጥቃት የሚውሉ በመረጃ መረብ የተሳሰሩ ቻት ቦቶች እና ለጥቃት የሚውሉ መተግበሪያዎች ደግሞ ሁለተኛው ምዕራፍ ነበር።
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ብቅ ያሉ ዳታ እና የመገልገያ መሳሪያን በሳይበር ጥቃት በመቆለፍ በምትኩ የመረጃው ባለቤቶች የተቆለፈባቸው መረጃ እንዲከፈትላቸው ክፍያ የሚጠየቁበት ወይም የራንሰምዌር ጥቃት እና በ2020ዎቹ የተጀመረው ውስብስብ የሳይበር ምኅዳር ላይ የሚፈጸሙ የመረጃ ጥቃቶች ናቸው፡፡
በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘው አምስተኛው የሳይበር ማዕበል ዋነኛ መለያ ባሕርያቱ የጥቃቱ ፍጥነት አና ስፋት፣ ዝግጁ የኾኑ የጥቃት መሣሪያዎችን መጠቀም መቻሉ እና እጅግ የተራቀቁ የማኅበራዊ ምሕንድስና (Social Engineering) ስልቶችን መከተሉ ነው።
አምስተኛው የጥቃት ማዕበል እንደ ጥልቅ ማታለለ (Deepfakes) ያሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎችን በመጠቀም የሰዎችን ምስል እና ድምፅ በማስመሰል ለማጭበርበሪያ ይጠቀሙበታል፡፡
እንዲህ አይነት መተግበሪያዎችን በዳርክ ዌብ ላይ በርካሽ የሚገኙ መኾኑ ደግሞ የጥቃት ማዕበሉ እንዲያብብ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ዳርክ ዌብ የምንለው እንደ ጉግል ባሉ በተለመደው የመረጃ ማሰሻ አማራጮች የማናገኘው የሳይበር ዓለም ነው። ቶር ተብሎ የሚጠራውን አይነት ማሰሻ ወይም ብሮውዘር በመጠቀም ልናገኘው የምንችለው ነው፡፡
በአዲሱ የጥቃት ማዕበል ምሥጢራዊ የቋንቋ ሞዴሎችም (Dark LLM) ያለገደብ ለጥቃት የሚውሉ መተግበሪያዎችን ለማምረት ግልጋሎት ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ምሥጢራዊ የቋንቋ ሞዴሎች (Dark LLM) የምንላቸው እንደ ቻት ጂፒቲ እና ጂሚናይ የሥነ ምግባር ገደብ የሌላቸው የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሳሪያዎች ናቸው። በአምስተኛው የሳይበር ጥቃት ማዕበል በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው፡፡
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባሉት ሁለት ስለቶቹ የችግር መቁረጫም የችግር መፍጠሪያም ኾኖ ቀጥሏል፡፡ ዋናው ነገር በሥነ ምግባር፣ በሰብዓዊነት እና በኀላፊነት መጠቀሙ ላይ ነው፡፡
ዘጋቢ:- ዘመኑ መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
