
ባሕር ዳር: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል የትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን የነቃ ዜጋን ለማፍራት የትምህርት ዘርፉ ቀዳሚ መኾኑን ተናግረዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ክልሉ በፈታኝ ችግር ውስጥ ኾኖም ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሰፋፊ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎችን ለመመለስ በትኩረት መሠራቱንም ገልጸዋል። ነገር ግን በዓመቱ እንዲማሩ በዕቅድ የተያዙ ተማሪዎች በሙሉ ማስተማር እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት።
የሰው ሃብት እና የግብዓት ማሟላት ላይም ባለፉት ወራቶች በትኩረት መሠራቱን አንስተዋል። 7 ሺህ 35 የሚኾኑ የመማሪያ እና የአሥተዳደር ክፍሎች መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል። ለመማሪያ መጻሕፍት ጥምርታም ትኩረት ተሠጥቶ መሠራቱን ነው የተናገሩት።
ለክልል እና ለሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ እና ተወዳዳሪ እንዲኾኑም ቢሮው አቅጣጫ ይዞ ሢሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በክልሉ ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች በፍጥነት እየተገነቡ መኾናቸውን ያነሱት ኀላፊው በ2019 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀምሩ ታስቦ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት ውስጥ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ማስፋት እና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ዋና ዋናዎቹ እንደኾኑም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው በስድስት ወራት 317 ሺህ 500 ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት።
ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱ ተማሪዎችን ለመመለስ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ባለፉት ወራት ችግር ውስጥ የወደቀውን ትምህርት ለመመለስ በተሠራው ሥራ ድጋፍ ላደረጉ አካላት እና ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
