ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ አመኔታ ጠባቂዎች ናቸው።

6
ባሕር ዳር፡ ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አዘጋጅነት 11ኛው የክልል እና የከተማ አሥተደደር ዋና ኦዲተሮች የጋራ ሙያዊ ምክክር እና ልምድ ልውውጥ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እንደዚህ አይነት የምክክር መድረክ የኦዲት ጥራትን እና ውጤታማነትን በማሳደግ በዋጋ ሊተመን የማይችል እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ አመኔታ ጠባቂዎች ናቸው ያሉት አፈ ጉባኤዋ በፍጥነት እያደገ ባለው የተቋማት በጀት፣ ውስብስብ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶች፣ የሕዝብ ተጠቃሚነት እና የተጠየቅ ፍላጎት መጨመር በውጤታማነት ለመወጣት የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች ሙያዊ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ወቅታዊ ዓለም አቀፍ የኦዲት ደረጃዎችን በተገቢው ተግባራዊ በማድረግ አገልገሎታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ግድ የሚላቸው ጊዜ እንደኾነም ጠቅሰዋል፡፡
በመድረኩ በፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት፣ በገቢ ኦዲት፣ በክዋኔ ኦዲት፣ በአካባቢ ኦዲት፣ በልዩ ኦዲት፣ የኦዲት ጥራት መረጋገጥ እና ምርምር ዙሪያ ቴክኒካዊ ውይይቶችን ይካሄዳሉ ብለዋል።
በዚህ የዲጂታላይዜሽን ዘመን ቴክኖሎጂን ለበለጠ ውጤታማ የኦዲት አገልግሎት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ጠቃሚ ተሞክሮዎች ልውውጥ እንደሚኖርም አንስተዋል፡፡
የዋና ኦዲተር ተቋማት ነጻ እና በዓለም አቀፉ የኦዲት ተቋማት መርህ መሠረትም ገለልተኝነትን በማስጠበቅ እንዴት ዜጎችን ማገልገል እንደሚገባም ምክክር ይካሄዳል ብለዋል፡፡
መድረኩ ውይይት ብቻ ሳይኾን በተቋሞች መካከል ጠንካራ የትብብር እና ለቀጣይ ሙያዊ ልህቀት መሰረት በመኾን የአገልግሎት ተጠቃሚ ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚረዳ እንዲኾን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየደባርቅ-ጃናሞራ መንገድ ግንባታን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።
Next articleወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።