ለአገው ፈረስ ባሕል ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

14
‎ባሕር ዳር: ጥር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአገው ሕዝብ ፈረስን ለእርሻ ሥራ፣ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን ለማድመቅ፣ ለሠርግ እና ለለቅሶ ማጀቢያ ይጠቀሙበታል፡፡
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ የፈረስን እና የአርበኞችን ውለታ ለመዘከር በ1932 ዓ.ም ሃሳቡ ተጠንስሶ በ1933 ዓ.ም በይፋ እንደተቋቋመ ይነገራል፡፡
‎ይህ ባሕል በየዓመቱ እየተከበረ መጥቶ ዘንድሮ 86ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል፡፡ የዘንድሮውን የአገው ፈረስ ባሕል በደመቀ ኹኔታ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የነገሩን የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዋና አለቃ የኾኑት አለቃ ጥላየ አየነው ናቸው፡፡
በዓሉ ጥር 23 ቀን ለ86ኛ ጊዜ የሚከበር መኾኑን አንስተው በዞን ደረጃ በትኩረት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
‎የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው በፊት ያልነበረ የተተኪ ወጣቶች የፈረስ ትርኢት የሚቀርብበት መኾኑ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ቁጥራቸው 200 የሚደርሱ ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 18 ዓመት ያሉ ተተኪ ወጣቶች የፈረስ ትርኢት እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል፡፡
በትርኢቱም ድንግል አሳ(የፈረሶች ጭፈራ)፣ ጭፈራ፣ ሰላምታ አሰጣጥ እና ስግሪያን ጨምሮ የተለያዩ የፈረስ ትርኢቶችን ለማቅረብ በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የሴት እና ዐይነ ስውር ፈረሰኞችም ትርኢት እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል፡፡
‎የፈረስ ማኅበሩ ከ62 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲኾን በዘንድሮው በዓል ከ5 ሺህ በላይ ፈረስ ጋላቢዎች የአይመሎ ትርኢት ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጋቸውን አለቃ ገልጸዋል፡፡ ፈረሰኞች ብቻ ሳይኾኑ የሕዝብ የኾነውን ባሕል ሌሎችም እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‎በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቃለአብ ካህሊ ለዘንድሮው የአገው ፈረሰኞች በዓል ጥር 23/2018 ዓ.ም ‘’የአብሮነት ቅርስ የሰላም ውርስ’’ በሚል መሪ መልዕክት በእንጅባራ ከተማ በድምቅት ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
‎በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚመራ ዐብይ ኮሚቴ በሥሩ የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በየጊዜው ተግባራት እየተገመገሙ ችግሮችን በመፍታት ሥራዎች እየተሠሩ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡
‎ባሕሉ በሚከበርበት ወቅት አካባቢውን ሳቢ እና ማራኪ እንዲኾን እና ባለሆቴሎች ተገቢውን አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ውይይት መካሄዱንም አንስተዋል፡፡
ለባሕሉ ከፍተኛ ቱሪስት ይገኛል ተብሎ ስለታሰበ የድንኳን ዝግጅት ሥራው እየተሠራ ነው፤ ለፈረስ ትርኢቱ ሜዳውን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
ባሕሉን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው በዕለቱ በቀጥታ ሥርጭት ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል፡፡
‎ከፈረስ ትርኢቱ በተጨማሪ የፓናል ውይይት፣ ዞናዊ የቁንጅና ውድድር፣ ባሕላዊ ምግብ እና መጠጥ፣ የአልባሳት፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች እና በየዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን የሚያሳይ ኤግዚቪሽኖች የፕሮግራሙ አካል እንደሚኾኑም ገልጸዋል።
‎የዘንድሮውን የአገው ፈረስ ባሕል ለየት የሚያደርገው ባሕሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተሠሩ ሥራዎችን ጫፍ ለማድረስ በተሠራበት ማግስት መኾኑ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ትልቅ ባሕል ላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እንዲታደሙ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleፈረሶቹ ጋላቢዎቻቸውን፣ ጋላቢዎቹም ፈረሶቻቸውን ያውቃሉ።
Next articleየመርቆሬዎስ በዓልን በተክሌ አቋቋም ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።