
ባሕር ዳር: ጥር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ከአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ጋር በመተባበር ”አካታች የጤና የትምህርት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የሰው ሠራሽ አካል ድጋፍ አገልግሎት በመዘርጋት የወጣት አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልዕክት አካል ጉዳተኞችን በሁሉም ዘርፍ ተደራሽ የማድረግ የንቅናቄ መድረክ አስጀምሯል።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬስብሀት ዘገየ ፌዴሬሽኑ ከአልማ ባገኘው ድጋፍ አካል ጉዳተኞችን የማብቃት ፕሮጄክት መጀመሩን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ፍሬስብሀት ገለጻ ፕሮጀክቱ 9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ተበጅቶለታል። ለአካል ጉዳተኞቹም የትምህርት እና ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ የጤና መድኅን ዋሥትና፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ እና የሰው ሠራሽ የአካል ድጋፍ ይደረጋል።
ንቅናቄው በክልሉ 23 ወረዳዎችም ይካሄዳል። ከአካል ጉዳተኞች ሰፊ ጥያቄዎች መካከል ውስኑን የመመለስ ጅማሮም ነው ብለዋል አቶ ፍሬስብሀት። አልማ አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ ያደረገውን ሥራ ሌሎችም እንዲከተሉት ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል 4 ሚሊዮን ገደማ አካል ጉዳተኞች አሉ። እስካሁን ድረስ የሥራ እና የትምህርት ዕድል ያገኙት ሁለት በመቶ ብቻ ናቸው። ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ ግን አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ እና ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት የሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ መብራት ይርሳው አካል ጉዳተኞች በትንሽ እገዛ ራሳቸውን ችለው መሥራት እና መኖር እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ምክር ቤታቸው አካል ጉዳተኞችን አካትቶ እንዲሠራ እንደሚከታተል ገልጸው በጎ አድራጊ ድርጅቶችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሴቶች ማደራጃ ባለሙያ ትዕግሥት ሙጨየ ለአካል ጉዳተኞች በተለይ ለሴቶች የሚደረገው ድጋፍ ማኅበረሰብን እንደመደገፍ መኾኑን ገልጸዋል።

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ይባቤ ሀብቱ የድጋፍ ፕሮጄክቱ የአካል ጉዳተኞችን አቅም እንደሚጨምር ገልጸዋል። አካል ጉዳተኞች የኅብረተሰቡ ክፍል መኾናቸውን ጠቅሰው መሥራት እንደሚችሉ እና ለመሥራት እንደማያንሱ በመገንዘብ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
