
ባሕር ዳር: ጥር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ ሰላም ያልተነገረበት ዓለም እና ዓውድ የለም። ወላጆች የልጆቻቸውን ስም ሰላም፣ ሰላማዊት፣ ሰላሙ ማለታቸው ሰላምን አብዝተው የመፈለጋቸው ማሳያም ይሆናል።
ከተሞችም ቢኾኑ ሀገረ ሰላም፣ ፍኖተ ሰላም ተብለው ሲጠሩ በምክንያት ነው። የሃይማኖት ቦታዎችን ሳይቀር ደጀ ሰላም፣ ደብረ ሰላም እና ማኅደረ ሰላም ማለትም እንዲሁ።
ብቻ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው ሲባል በተግባር ጭምር ነው። ባለፉት ዓመታት በሰላም እጦት ምክንያት በአማራ ክልል በርካታ ቁሳዊ እና አካላዊ ጉዳት ደርሷል።
ከዚህ አሰቃቂ ችግር ለመውጣት ታድያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ስለሁለንተናዊ ደኅንነት ሲባል የሰላም ጥሪ እየተደረገላቸው ይገኛል። በርካታ ታጣቂዎችም የሰላም ጥሪውን እየተቀበሉ ነው።
በደቡብ አቸፈር ወረዳ የጤና ባለሙያ የኾነው የዛሬ ባለታሪካችን ወጣት ከዚህ በፊት ታጥቆ በጫካ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። አሁን ደግሞ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ ስለ ሰላም እየሠራም ይገኛል።
ወጣቱ ከአሚኮ ዲጂታል ጋር በነበረው ቆይታ “ዕውነት አለ መስሎኝ ወጥቸ ነበር፤ አቅጣጫውን ሲስት ግን ተመልሻለሁ” ብሏል።
እኔ የሰላምን መንገድ የመረጥኩት በጥልቀት አስቤበት እና ትርፍ እና ኪሳራውን አስልቸ ነው ይላል ወጣቱ።
የሕገ ወጥነት ተግባሩን እንደ ዕድል በመጠቀም የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩ አካላት እና ወንጀለኞች ጭምር ያሉበት የተሳሳተ ትግል ነው ብሏል።
ከወንጀለኛ ጋር የአማራን ጥያቄ የምናስመልስበት ዕድል ባለመኖሩ ሰላምን መርጫለሁ፤ አሁንም ለሰላም አበክሬ እየሠራሁ እገኛለሁ ሲል ለአሚኮ ተናግሯል።
ይባስ ብሎ ደግሞ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብረው የሚሠሩ እንዳሉም በተግባር በማየቴ ሰላምን መረጥኩ ነው ያለን።
ከጓደኞቸ ጋር የወሰንኩት ውሳኔ ልክ ነበር የሚለው ወጣቱ አሁን ላይ ወደነበረበት የመንግሥት ሥራ ተሠማርቶ እየሠራ እንደኾነ ነግሮናል።
መንግሥት የማቋቋሚያ እና የድጎማ ስጦታም እያበረከተ እንደኾነ ጠቁሟል።
አሁንም በጫካ ባላወቁት ነገር ገብተው በእገታ እና በስቃይ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን እንዳሉ መረጃው አለን የሚለው ወጣቱ እንደምንም ወደ ሰላም ቢመጡ መልካም ነው ይላል።
ምሁራኖች ሳይቀር ዋሻ ውስጥ ታጉሮባቸው እንደሚገኙ መረጃው አለን ብሏል። ወደ ሰላም በመመለስ ቤተሰብን መምራት እና ከአጓጉል መስዋዕትነት መትረፍ ብልህነት እንደኾነም አስረድቷል።
ባሳለፍናቸው ዓመታት በኢኮኖሚ ከመጎዳት እና ወንድሞቻችን ከማጣት ውጭ ያተረፍነው የለም ብሏል። ለዚህም በቤተሰቦቸ ላይ የደረሰው ግፍ ምስክር ነው ይላል። “ለአማራ መታገል ማለት አማራን ማሰቃየት ከኾነ ይቅር ነው” ያለው።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ለሦሥተኛ ዙር የቀድሞ ታጣቂዎች ምርቃት እና የሽኝት መርሐ ግብር ላይ የቀድሞ ታጣቂ ኀይሎችን በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በተለያዩ ዘርፎች መልሶ ማቋቋም ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ፉክክር እና ግድያን በማራቅ የሰላምን አማራጭ በመቀበል የክልሉን ሕዝብ መካስ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
