
አዲስ አበባ፡ ጥር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመኾን እየተገበረ ያለውን የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የግማሽ ዓመት ግምገማ ከተለያዩ ክልሎች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር መገምገም ጀምሯል።
ፕሮጀክቱን ለመፈጸም የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው እንደ አውሮፖውያኑ አቆጣጠር በ2021 ሲኾን ተግባራዊ የኾነው በ2023 መኾኑን በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ኀላፊ ከበሩ በላይነህ አስታውሰዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ በቀለ የምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በተጣጣመ መልኩ እየተተገበረ ያለ እና እስከ ወረዳ ድረስ ውጤት እየታየበት ያለ ፕሮጀክት መኾኑን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ፣ በኔዘርላንድ መንግሥት፣ በጀርመን የልማት ድርጅት፣ በስፓኒሽ ትብብር እና በሌሎች አጋር አካላት ትብብር በመተግበር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ያሻሽላል ተብሎ እየተተገበረ ያለው ፕሮግራሙ የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ግምገማውን ለቀጣይ ሦሥት ቀናት በማከናወን ለቀጣዩ ግማሽ አመት የትግበራ ዘመን ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ የዓለም ባንክ ተወካይ ካሪሽማ ዋስቲንን ጨምሮ የፕሮግራሙ ዋና አጋሮች ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለ
