
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2018ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከሚከበሩ የጥርን በባሕር ዳር ዝግጅቶች ውስጥ “የሰባሩ ጊዮርጊስ” ክብረ በዓል አንዱ ነው።
ታቦተ ሕጉ ከመንበሩ ወጥቶ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች ተከብሯል። በጣና ሐይቅ ላይ በጀልባ እና በታንኳ ታጅቦ አካባቢውንም ባርኳል።
የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም ለምዕመኑ ቡራኬ ሰጥተዋል። አማኙ ጽናትን በመላበስ ፍቅርን መማር ይገባዋል ብለዋል።
ጥላቻ፣ ሐሜት እና በሀሰት መመስከር ከክርስቶስ ፍቅር የሚለይ በመኾኑ የሃይማኖት ተከታዮች ለሃይማኖታዊ ግብረገብ ተገዥ መኾን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። በመከባበር፣ በፍቅር እና በአንድነት መኖርን ማጠናከርም ይገባል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው እንደገለጹት ደግሞ ጥርን በባሕር ዳር በድምቀት ከሚከበሩት ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ “የዝርወተ አጽሙ ሰባር ጊዮርጊስ” ክብረ በዓል አንዱ ነው።
ጥርን በባሕር ዳር መርሐ ግብር ከተጀመረ ጀምሮ የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት። በዓሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ከማሳደግ ባለፈ ማኅበራዊ መሥተጋብርን እና የሀገርን ገጽታን በማጠናከር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተም ይገኛል ብለዋል። ይህንን ሃይማኖታዊ እሴት ይበልጥ ለማሳደግ እየተሠራም ይገኛል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
