
ጎንደር: ጥር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መኾናቸውን የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መሪዎች እና አባላት አስታውቀዋል።
ነፍጥ አንግበው ጫካ በመግባት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አባላት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እየገቡ ይገኛሉ።
የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የአፋሕድ መሪዎች እና አባላት በጎንደር ከተማ የተሠሩ የልማት ተግባራትን በመስክ ምልከታ አረጋግጠዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ የፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳትን፣ ከአዘዞ ፒያሳ የተሠራውን የኮሪደር ልማት እና በከተማዋ በግሉ ዘርፍ ተሠማርተው ውጤታማ የኾኑ ግለሰቦችን ተሞክሮ ተመልክተዋል።
የልማት ሥራዎች በአጭር ጊዜ የተሠሩ መኾናቸውን ያነሱት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ወታደራዊ አሥተዳደር መምሪያ ኀላፊ የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተ ናቸው። የልማት ሥራዎቹ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና ልማት እንዲቀጥል የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ የቀድሞው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ የነበሩት መልካሙ ጣሴ ናቸው።
ክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በግጭት ውስጥ ኾኖ ይህን ያህል የልማት ሥራዎችን መከወን ከቻለ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ቢሰፍን ከዚህም የበለጠ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ ነውም ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ጉብኝቱ በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆዩ እና የሰላም አማራጭን በመቀበል የገቡ አካላት ጎንደር ከተማ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ እንዲመለከቱ ዕድል የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል።
ጎንደር ከተማ አሁንም የምትፈልጋቸው በርካታ የልማት ጥያቄዎች ያሉ በመኾኑ ለሰላም ሁሉም ቅድሚያ በመስጠት ለከተማዋ ተጠቃሚነት በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ: ቃልኪዳን ሃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
