በአማራ ክልል መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የዘላቂ ስምምነት ማዕቀፍ ውጤታማ ለማድረግ የማስፈጸምያ ስምምነት ሥነ ሥርዓት ተካሄደ።

91
ባሕር ዳር፡ ጥር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኅዳር 25/2018 በክልሉ መንግሥት እና በአፋሕድ መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት መሰረት ያደረገ እና ከስምምነቱ በኋላ የተከናወኑ ተግባራት እና ቀጣይ መኾን ስላለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት የስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ተደርጓል።
ስምምነቱ በዋነኛነት ኅዳር 25/2018 ዓ.ም የተካሄደው አፈጻጸም እንደተጠበቀ ሆኖ በስምምነቱ ዝርዝር አፈጻጸም ሂደቶች፣ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ የማቋቋም አካሄድና የቁጥጥር እና ክትትል ኅላፊነትና እንዲሁም በዋናው ሰነድ ያልተካተቱ ድምጾች አልተሰማንም ያሉ ጉዳዮችን የተመለከተ ነው።
ይህ የማስፈጸምያ ስምምነት በፌዴራል መንግሥት አመቻችነት በተለይም በሰላም ሚኒስቴር፣ በመከላከያ ሠራዊት እና በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አስተባባሪነት የተደረገ ሲኾን በአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) እና በአፋሕድ ወታደራዊ አሥተዳደር ኀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተ መካከል የስምምነት ፊርማ ተደርጓል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ይህ ዘመን የሀገርን በጋራ ለማሳደግ የምንተባበርት እንጅ በመገዳደል የምናሳልፍበት መኾን የለበትም ብለዋል።
ዘመኑ በጋራ በመተባበር ከሌሎች ሀገራት ተርታ በመሰልፍ ያለንበት ዘመን በመኾኑ ሀገራችንን ለመበተን ከሚሠሩ አካላት ጋር መተባበርን በመተው ወደ ሰላም አማራጭ መምጣት አለብን ነው ያሉት።
መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጀመረውን መንገድ በመከተል ወደ ስምምነት መምጣት ትውልድን ከጦርነት የማዳን አንዱ ስልት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ስለሆነም ትውልዱን በታሪክ ተወቃሽ ላለማድረግ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን መምረጥና በጦርነት የሚወድምን ሃብት እና ንብረት የማትረፍ ኀላፊነት ያለብን በመኾኑ ሌሎች በጫካ ያሉ ተዋጊ ኃይሎችም የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንዲመጡ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፋህድ ምክትል ሊቀመንበርና ወታደራዊ አዛዥ ኮሎኔል ፋንታው ሙሃባው ባደረጉት ንግግር ደግሞ
ከሦሥት ዓመት በፊት ወደ ጫካ ለመግባት የተገደድነው የአማራን ሕዝብ ግፍና መከራ ለማስቀረት ነበር ብለዋል።
ወደጫካ ስንገባ ምክንያት እንደነበረን ሁሉ ወደ ሰላም አማራጭ ስንመጣም ምክንያት አለን ያሉት ኮሎኔሉ የሰላም ውይይቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል በማለት በአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ አባላት በዳውንት ወረዳ የተደረገውን ስምምነት አስታውሰዋል።
በመኾኑም ስምምቱ የታሰበበት እንጅ ሌሎች እንደሚሉት የአማራን ሕዝብ የመክዳት አለያም እጅ የመስጠት አይደለም ብለዋል።
ለትግል የወጣነው የአማራን ሕዝብ ለማዳን ቢኾንም ባለፉት ሦሥት ዓመታት የክልሉ ሕዝብ በጦርነት ውስጥ መከራ እያስተናገደ በመኾኑ ይህ መከራ እንዲቆም ጦርነት አስፈላጊ ባለመሆኑ የሰላም አማራጭ ተቀብለናል ብለዋል።
ወደ ሰላም ስምምነት እንድንመጣ ያደረገን ሌላው የፋኖ ኃይል ከሻዕቢያ እና ከሕወሃት ጋር ተባብሮ ሀገር እንዳይረጋጋ በማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ የሚደረግለት በመኾኑ ከእነሱ ጋር የመተባበር እና ሀገርን የመክዳት ፍላጎት መቀበል ስለማንፈልግ የአማራን ሕዝብና ኢትዮጵያን ለማዳን የሰላም አማራጭ ተቀብለናል ብለዋል።
የአማራ ክልልን ሕዝብ ችግር ለመፍታት ከግብጽና ሻዕቢያ ጋር በመወገን ሳይኾን ከፌዴራልና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመኾን መፍትሔ ማበጀት የግድ በመኾኑ ነው የጠቀሱት።
የአፋህድ ወታደራዊ አሥተዳደር መምሪያ ኀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተ ባደረጉት ንግግር ደግሞ የአማራ ክልልን ሕዝብ ችግር ለመፍታት ጦርነት አማራጭ ባለመኾኑ እና ጦርነቱ ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ በመግባቱ ለሕዝቡ ሰላም ስንል ስምምነት አድርገናል ብለዋል።
የትግሉ ዓላማ የክልሉን ሕዝብ ከማዳን ይልቅ በሌሎች ኃይሎች ምክንያት በፋኖ ስም ቀጠናውን ማተራመስ ስለሆነ ይህን በመቃወም ሕዝቡን ለማዳን ስንል ተስማምተናል ብለዋል።
ሌሎች የፋኖ ኃይሎች ወደዚህ የሰላም ስምምነት እንዲመጡ ጥሪ ያቀረቡት ረዳት ፕሮፌሰሩ ብሔራዊ ጥቅምን ከሚጎዱ ኃይሎች ከመተባበር ይልቅ ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሥራት የሕዝብን ጥያቄ ማስመለስ ይኖርብናል ብለዋል።
በመሆኑም የቀጣናውን ትርምስ ከግምት ውስጥ በማስገባት የትግል ስልታችንን በሰላማዊ መንገድ ማድረግና የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር እንሠራለን ብለዋል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የአማራ ክልልን ቀውስ ለማስቆም ኅዳር 25/2018 ዓ.ም የተደረገው የሰላም ስምምነት ትልቁ የታሪክ እጥፋት ኾኖ በታሪክ ይቀመጣል ብለዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ይህ የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ከጦርነት ይልቅ ሰላም ይሻላል በሚል ወደ ሰላም አማራጭ የመጡ የአፋህድ አባላትን አመሰግነዋል።
የፋኖ ኃይሎች “የአይጥና የድንቢጥ ጉባኤ” በማድረግ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ ብሎም የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ ለባእዳን በመስጠት ተጠምደዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በመኾኑም ይህን የጠላት ሴራ አልቀበልም ያሉ እና ቀጣናዊ አሰላለፉን በመረዳት ወደ ሰላም መምጣታቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል።
ይህ ስምምነት በክልሉ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ጠመንጃ የምንዘቀዝቅበት፣ በክልሉ የተፈጠረውን ውድመት መልሶ ለመገንባት እና የሕዝቡን እሴት ወደ ነበረበት ለመመለስ መነሻ ነው ብለውታል።
በቀጣይም የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለመመለስ በአንዴ የሚሳካ ባለመሆኑ ፍላጎቶቻችንን በመግታት ለሕዝብ ሰላም መጽናት የእኛን ጀግንነት፣ ስክነት እና ብስለት ይጠይቃል ነው ያሉት።
ሌሎች በትግል ውስጥ ያሉ ኃይሎች የክልላቸውን እና ሀገራቸውን ቁመናና ወርድ ተገንዝበው ለክብራቸው ሲሉ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ በድጋሚ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleደብረ ታቦር ለቅዱስ መርቆርዮስ በዓል ተሰናድታ እንግዶቿን እየጠበቀች ነው።
Next articleየደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ክፍተት በአካባቢ እና በሕዝብ ጤና ላይ ጉዳት እያስከተለ ነው።