ደብረ ታቦር ለቅዱስ መርቆርዮስ በዓል ተሰናድታ እንግዶቿን እየጠበቀች ነው።

37
ባሕር ዳር: ጥር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ መርቆርዮስ በዓልን እና የፈረስ ጉግሥ ትርኢትን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ገልጿል፡፡
የመምሪያው ኀላፊ አለበል ደመላሽ እንደተናገሩት ዘንድሮም በዓሉን በድምቀት ለማክበር እየተሠራ ነው።
የመርቆርዮስ በዓል በፈረስ ሰልፍ፣ ውድድር፣ ትርኢት እና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ነው የሚከበረው።
በደብረ ታቦር ከተማም በዓሉ ጥር 25 ቀን በአጅባር ሜዳ ላይ በሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች ደምቆ ይከብራል።
የፓናል ውይይት፣ ባሕላዊ አለባበስ፣ የባሕላዊ ምግብ እና መጠጥ አውደ ርዕይ እንዳለም አቶ አለበል ተናግረዋል።
በዓሉ የማንነት መገለጫ፣ ታሪክን የሚዘክር እና የቱሪስት መስህብም ስለኾነ ከተማ አሥተዳደሩም በባለቤትነት እያከበረው መኾኑን አንስተዋል።
የከተማው እና የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይም ወጣቶች ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመተባበር በዓሉን ለማክበር እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል።
የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ለበዓሉ ስኬታማነት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፤ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድም ዝግጁ ነን ብለዋል። የጸጥታ ችግር እንዳይኖርም ኾነ በመገፋፋት ጉዳት እንዳይደርስ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ የሚሠራበት አደረጃጀት መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
ጎብኚዎች በበዓሉ እንዲታደሙ እና መገኘት ያልቻሉትም በሚዲያ እንዲከታተሉም ጋብዘዋል።
የመንበረ ንግሥት ልጅቱ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አሥተዳዳሪ እና የበዓል አከባበሩ የከንቲባ ኮሚቴ አባል የኾኑት መልዓከፀሐይ መሪጌታ እሸቱ እርቁ በቤተ ክርስቲያን በኩልም ካለፈው ዓመት የበዓል አከባበር ግምገማ ጀምሮ ወቅታዊውን ኹኔታ ጭምር ግምት ውስጥ በማስገባት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ባሕላዊ ክዋኔዎችም ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ጋር እንዲጣጣሙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በዓሉ በመጤ ድርጊቶች እንዳይዋጥ ዝግጅት መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
ከከንቲባ ኮሚቴ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
በዓሉ ሰላማዊ እንዲኾን ወጣቶች በባለቤትነት እንዲያስተባብሩ ኀላፊነት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ኅብረተሰብ ለበዓሉ ሰላማዊነት ትኩረት እንዲሰጥ እና ኀላፊነቱን እንዲወጣም አደራ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጥርን በባሕርዳር አካል የሆነው የታንኳ ቀዘፋ ውድድር እየተካሄደ ነው።
Next articleበአማራ ክልል መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የዘላቂ ስምምነት ማዕቀፍ ውጤታማ ለማድረግ የማስፈጸምያ ስምምነት ሥነ ሥርዓት ተካሄደ።