
ባሕር ዳር: ጥር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዲጂታል 2030 ጅማሮ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ካለው ነገር የመጀመሪያው ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ፋይዳ የዲጂታል ጉዞውን እያሳለጠ የሚገኝ መሳሪያ ነው፡፡
ተቋማት ቀልጣፋ እና ወጭ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲሰጡ በማገዝ ላይ ነው፡፡ በመኾኑም ባንኮች ወጥ በኾነ መንገድ ደንበኞቻቸውን ለመለየት ይችሉ ዘንድ ከሥርዓታቸው ጋር ፋይዳን የማስተሳሰር ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
የፋይዳ መታወቂያ ከባንኮች ጋር እንዲተሳሰር በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ እየተፈጸመ ያለ ሲኾን የፋይናንስ ተቋማት ወጥ የኾነ የመታወቂያ አጠቃቀም እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ መኾኑን በብሔራዊ መታወቂያ ኘሮግራም የባለድርሻ አካላት እና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የኾኑት ሳሚናስ ሰይፉ ከአሚኮ ዲጂታል ጋር በስልክ በነበራቸው ቃለ መጠይቅ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ ባንኮች ደንበኞቻቸው በአካል ወደ ቅርንጫፍ ሳይመጡ የፋይዳ መታወቂያቸውን የሚያስተሳስሩበትን ማስፋንጠሪያ እያጋሩ ስለኾነ በዚህ አማራጭ መጠቀም እንደሚቻልም አስረድተዋል::
ከባንኮች ጋር ለማስተሳሰር ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ቀድሞ መፈጸም ተገቢ መኾኑንም ተናግረዋል::
ፋይዳ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ሲተሳሰር ከወረቀት ወደ ዲጂታል አማራጭ ሽግግር ይፈጥራል። ፋይዳ ማጭበርበር እና ከማጭበርበር ጋር የተያያዙ እክሎችን ያስቀራል። በተቋማት እና በዜጎች መካከል መተማመን ይፈጥራል እንዲሁም ደንበኞችን በልዩነት ለመለየት ያስችላል በማለት ጥቅሞቹን ዘርዝረዋል፡፡
በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ላይ ያሉ መረጃዎች ለሌላ ተቋም ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ የመረጃው ባለቤቶች በሚላክላቸው የይለፍ ቃል መፍቀድ የሚጠበቅባቸው በመኾኑ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ እና ወጭ ቆጣቢ አማራጭ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በፋይዳ ቋት ላይ የሚቀመጡ የግል መረጃዎች ተመስጥረው የሚቀመጡ በመኾናቸው ሚስጥራዊናታቸው የተጠበቀ መኾኑን አቶ ሳሚናስ ገልጸዋል።
ለባንክ ማስተሳሰሪያም ኾነ ሕጋዊ ማንነትን ለማረጋገጥ ሁሉም የፋይዳ አማራጮች በሕግ ፊት እኩል ተቀባይነት ያላቸው በመኾኑ ሰዎች ግዴታ የፋይዳ መታወቂያን አትመው መያዝ አይጠበቅባቸውም፡፡
ነገር ግን ከፕሮግራም ማዕከሉ የተላከላቸውን ቁጥር በመጠቀም፣ በዲጂታል ኮፒ በመያዝ አሊያም ቁጥሩን በወረቀት ጽፎ ለአገልግሎት መጠቀም የሚቻል መኾኑን አቶ ሳሚናስ አስረድተዋል።
የዲጀታል መታወቂያ ፕሮግራም 32 ሚሊዮን የሚኾኑ ዜጎችን በቋቱ መዝግቦ የዲጀታል መታወቂያ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ በተጨማሪም 100 ከሚኾኑ ተቋማት ጋር የትስስር ሥርዓት ፈጥሯል። ከእነዚህ ውስጥ 32ቱ ባንኮች መኾናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
